ማንቺስተር ሲቲ ከተጫዋቾች ሽያጭ ከፍተኛ ገቢ ያገኝ የእንግሊዝ ክለብ ነው
የ2024/25 የዝውውር መስኮት ግብይት ምን ይመስላል?
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ2024/25 የተጨዋቾች ዝውውር መስኮት ትላንት ሌሊት ተዘግቷል።
የእግር ኳስ ዝውውር መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከቅርብ ተከታዩ የጣሊያን ሴሪኣ ከእጥፍ በላይ ወጪ አፍሷል።
በዚህም በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከ1.96 ቢሊዮን በላይ ፓውንድ ወጪ መደረጉን ነው ቢቢሲ ያስነበበው።
የተጠናቀቀው የዝውውር መስኮት፣ ስምንት የእንግሊዝ ክለቦች የራሳቸውን የዝውውር ወጪ መዝገብ ጣራ ከፍ ያረጉበት ነው።
ለመሆኑ ከንግድ አንፃር ውጤታማ ሥራ የሠሩት የትኞቹ ናቸው? ትልልቆቹ ውሎች በእነማ ተፈፀሙ? ምንም ያላወጡትስ ቡድኖች እነማን ናቸው ?
በሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪ ክለቦች ያወጡት ወጪ
የዋንጫ ባለድሉ ማንችስተር ሲቲ ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች የክረምት ዝውውር ዝቅተኛ ወጪ ያስመዘገበ ክለብ ሲሆን በአንጻሩ ከተጫዋቾች ሽያጭ 118.5 ሚሊዮን ፓውንድ ትርፍ ወደ ካዝናው አስገብቷል።
ለብራዚላዊው የክንፍ ተጫዋች ሳቪንሆ ዝውውር 21.4 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጡት ማንችስትር ሲቲዎች፣ አጥቂው ጁሊያን አልቫሬዝ ፣ ተከላካዮቹን ጆኣዎ ካንሴሎ እና ቴይለር ሃርዉድ ቤሊስን በመሸጥ ትርፋማ ሆነዋል።
በርግጥ ያለፈው ውድድር አመት እስከ ሶስተኛ ያጠናቀቁት ክለቦች ከተጣራ ወጪ አንፃር ሲታይ የአንዳቸውም ከፍተኛ አይደለም።
አርሰናል ለሁለት ተጫዋቾች ለሪካርዶ ካላፊዮሪ እና ሚካኤል ሜሪኖ ግዢ 93.9 ሚሊዮን ፓውንድ ቢያወጣም ከሺያጭ 76.8 ሚሊዮን ፓውንድ አግኝቷል።
ሊቨርፑል የተከላካይ መስመር ተጫዋቹን ፌድሪኮ ቺዬሳ እና ግብ ጠባቂ ጂዎርጂ ማማርዳሽቪሊን ሲገዛ፤ ፋቢዮ ካርቫልሆ ፣ ሴፕ ቫን ደን በርግ እና ቦቢ ክላርክን ሸጦ 14.4 ሚሊየን ፓውንድ ትርፍ አግኝቷል፡፡
ቶድ ቦዬህሊ ክለቡን በባለቤትነት ከተረከቡ በኋላ ከግንቦት 2022 አንስቶ ወጪው ከ1.3 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የተተኮሰው ቼልሲ በዝውውር መስኮቱ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ከገዛቸው 10 ተጫዋቾች በላይ 12 ተጫዋቾችን የሸጠው ቡድኑ ከ203 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አፍስሷል፡፡
በዝውውሩ በተጫዋቾች ሽያጭ ያገኝው ገንዘብ እና ያወጣው ወጪ ሲቀናነስ 46.5 ሚሊየን ፓውንድ የተጣራ ወጪ በፕሪሚየር ሊጉ ካሉ 12 ክለቦች ከፍተኛ ወጪ ካወጡት መካከል ይጠቀሳል፡፡
ብራይተን የዝውውር መስኮቱ ከፍተኛው ገንዘብ አውጪ
ብራይተን 195.7 ሚሊዮን ፓውንድ ለ9 ተጫዋቾች ከካዝናው አውጥቶ ፣ ስድስት ተጫዋቾች በማሰናበት 42.1 ሚሊየን ፓውንድ ገቢ ቢያገኝም፤ በ153.6 ሚሊዮን ፓውንድ የተጣራ ወጪ የፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ አውጪ ክለብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
107.6 ሚሊዮን ፓውንድ ያፈሰሰው በዘንድሮው አመት ወደ ሊጉ ያደገው ኢፕስዊች ተከታዩ ከፍተኛ ገንዘብ አውጪ ነው፡፡
የክለባቸውን የዝውውር መዝገብ ጣራ በመሰባበር ብራይተን ብቸኛው ክለብ ግን አይደለም፡፡ በርንማውዝ አጥቂው ኢቫኒልሰንን ለመመልመል 31.7 ሚሊዮን ፓውንድ የመጀመሪያ ክፍያ ፈጽሟል፡፡
ብሬንትፎርድ በበኩሉ ኢጎር ቲያጎን በ30 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያስፈርም፤ ፉልሃም የአርሰናሉን ኤሚሌ ስሚዝ በ27 ሚሊየን ፓውንድ መነሻ ክፍያ ወደ ክለቡ ቀላቅሏል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ አስቶን ቪላ ፣ ኢፕስዊች ፣ኖቲንግሃም ፎረስት እና ቶትንሃም የራሳቸውን የዝውውር ውጪ መጠን መዝገብ ከፍ ያደረጉ ተጨማሪ ክለቦች ናቸው፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን ዘንድሮ የተቀላቀሉ ክለቦች 300 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ያፈሰሱበት ዝውውር
ሶስት አዳጊ ክለቦች በሊጉ የመቆየት እድላቸውን ለማሳደግ ቀላል የማይባል ገንዘባቸውን አፍስሰዋል፡፡
ኢፕስዊች እና ሳውዝሃምፕተን ሁለቱም ከ100 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ሲያወጡ ሌስተር ሲቲ ከ75 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ከፍሏል፡፡
ከ109 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ለአስር ተጫዋቾች ወጭ ያደረገው ኢፕስዊች ሰባቱ ተጫዋቾች ከፕሪሚየር ሊጉ ያዛወራቸው ናቸው፡፡
ሌስተር በአንጻሩ በተለየ ሁኔታ ከትላልቅ ሊጎች ተጫዋቾችን መልምሏል፡፡ ሰባት ተጫዋቾችን ያዘዋወረው ሌስተር አራቱን ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ቀሪዎቹን ደግሞ ከጣሊያን ፣ ፖርቹጋል እና ቤሊጂየም ሊጎች አንድ አንድ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡