ሩሲያ ከዩክሬን ስንዴ ጉዞ ስምምነት ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ስንዴ ዋጋ የ5 በመቶ ጭማሪ አሳየ
ተመድና ቱርክ የዩክሬን ስንዴ ለዓለም ገበያ እንዲደርስ በሚል ከሩሲያ ጋር ስምምት ላይ ደርሰው ነበር
በዚህ ስምምነት መሰረት 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከዩክሬን ወደ ሌሎች ሀገራት ተጓጉዟል
ሩሲያ ከዩክሬን ስንዴ ጉዞ ስምምነት ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ስንዴ ዋጋ የ5 በመቶ ጭማሪ አሳየ፡፡
ከተጀመረ ስምንት ወራትን ያስቆጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆን የጦርነቱ አካባቢ በዓለም ምግብ አቅርቦት ላይ እክል ፈጠርሯል፡፡
በተለይም ዩክሬን ስንዴ ወደ አፍሪካ እና እስያ ሀገራት በመላክ ዋነኛ ምግብ አቅራቢ ሀገር መሆኗን ተከትሎ ሀገራት እና የረድዔት ድርጅቶች የስንዴ መተላፊያ የሆነው ይቁር ባህር ከጦርነት ቀጠና ነጻ እንዲሆን ሲወተውቱ ነበር፡፡
በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ቱርክ ከሩሲያ እና ዩክሬን ጋር ባደረጉት ስምምነት ላለፉት ሁለት ወራት 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ስንዴ የምግብ አቅርቦት ችግር ወዳለባቸው አካባዎች መጓጓዙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና ባሳለፍነው ሳምንት ሩሲያ ከዚህ ስምምነት ራሴን አግልያለሁ ያለች ሲሆን ዩክሬን በክሪሚያ የባህር መሰረተ ልማቶች ላይ የድሮን ጥቃት ሰንዝራለች በሚል ነው፡፡
በዚህም መሰረት ዋነኛ የስንዴ መተላለፊያ የሆነው የጥቁር ባህር ደህንነቱ አስተማማኝ ባለመሆኑ ስንዴ ጭነው በሚጓዙ መርከቦች ላይ ጥቃት ሊደርስ ስለሚችል ከስምምነቱ መውጣጧን አስታውቃለች፡፡
አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረት እና ተመድ ሩሲያ ወደ ስምምነቱ እንድትመጣ የጠየቁ ሲሆን ሩሲያ እስካሁን ወደ ስምምነቱ መቼ እንደምትመጣ አላሳወቀችም፡፡
ሩሲያ ከዚህ ስምምነት መውጣቷን ተከትሎ የዓለም ስንዴ ዋጋ በ5 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል የተባለ ሲሆን በቆሎ ደግሞ በ2 ነጥብ 2 በመቶ አኩሪ አተር ደግሞ የአንድ በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተገልጿል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያ ላይ ያደረሰችው የድሮን ጥቃት አለመኖሩን ገልጻ ሞስኮ ስምምነቱን ለማቆም ምክንያት ስትፈልግ እንደነበር በፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በኩል አስታውቃለች፡፡
ዓለም በሩሲያ ላይ ጫና እንዲያደርግ የጠየቁት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ በዛሬው ዕለት ብቻ 16 መርከቦች መስተጓጎላቸውንም ጠቁመዋል፡፡