ፖለቲካ
ከዩክሬን ስንዴ ጭነው ከወጡ 87 መርከቦች ውስጥ 85ቱ ወደ አውሮፓ ሀገራት መጓጓዛቸው ተገለጸ
ምዕራባዊያን ሃገራት ለተቀረው ዓለም የማይጨነቁ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 196ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
ከዩክሬን ስንዴ ጭነው ከወጡ 87 መርከቦች ውስጥ 85ቱ ወደ አውሮፓ ሀገራት መጓጓዛቸው ተገለጸ።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በምስራቅ የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ባደሩጉት ንግግር ምዕራባውያን ሀገራት ራስ ወዳዶች መሆናቸው ገልጸዋል።
ለራሳቸው ፍላጎት ካልሆነ በቀር ለተቀረው ዓለም ግድ የላቸውም ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዓለማችን ወደ ብዙ ችግሮች እየገባች ያለችው በነዚህ ምዕራባውያን ሀገራት ምክንያት እንደሆነም አክለዋል።
ሩሲያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት ምክንያት በማድረግ በሞስኮ ላይ የጣሏቸው ማዕቀቦች ለዓለም ምግብና ነዳጅ ዋጋ መጨመር ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተናግረዋል ።
ሩሲያ በተመድ እና ቱርክ አደራዳሪነት መሰረት የምግብ ችግር ወዳለባቸው ሀገራት ስንዴ እንዲጓጓዝ ብታደርግም አብዛኞቹ የስንዴ መርከቦች የምግብ ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች ሳይሆን ወደ አውሮፓ መጓጓዛቸውንም ተናግረዋል።
ለአብነትም ከዩክሬን ስንዴ ከተጫኑ 87 መርከቦች መካከል 85ቱ ወደ አውሮፓ ሀገራት ተጓጉዘዋል ተብሏል።
ሁለት መርከቦች ብቻ ግን የምግብ ችግር አለበት ወደ ተባለው አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መጓጓዛቸውን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
አብዛኞቹ የአውሮፓ ሀገራት እንደ ቅኝ ገዢ ሀገር ይንቀሳቀሳሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ግን ነገሮች እነሱ ባሰቡት መንገድ አይቀጥልም የስንዴ ማጓጓዙ ስራም ገደብ ይጣልበታል ሲሉም አክለዋል።
የቡድን ሰባት ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን ማውጣታቸው ይታወሳል ።
ይሁንና ሩሲያ በበኩሏ የቡድን ሰባት ሀገራትን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ህብረቱ በሩሲያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ካላነሳ ነዳጅ ወደ አውሮፓ ሙሉ ለሙሉ መላኳን አቁማለች።