የተመድ ዋና ጸሃፊ በኢትዮጵያ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
ጉቴሬዝ የተኩስ አቁም ስምምነት “በኢትዮጵያውያን መካከል ውይይት” ለማድረግ የሚያስችል መሆን አለበትም ብሏል
የኢትዮጵያ መንግስት ካለፍነው ከሰኔ ጀምሮ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ እንደነበረ ይታወሳል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
ጉቴሬዝ ጥሪውን ያቀረቡት በደቡብ አሜሪካዋ የኮሎምቢያ መዲና ቦጎታ በተከበረው የመንግስት እና አማጽያን የሰላም ስምምነት 5ኛ ዓመት ላይ ተገኝተው መሆኑን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
በኮሎምቢያ በታጣቂዎችና መንግስት መካከል ለስድስት አስርት ዓመታት የዘለቀውና ለ9 ሚልየን ንጹሃን ዜጎች ህልፈት ምክንያት ደም አፋሳሽ ግጭት ካበቃና ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ስምምነት ከመጡ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የሰላም ስምምነቱን 5ኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገረ ኮሎምብያ የተገኙት ጉተሬዝ “በኮሎምቢያ ያለው የሰላም ሂደት፤ ኢትዮጵያን ለመታደግ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለግጭቱ ዋና ተዋናዮች ዛሬ አስቸኳይ ጥሪ እንዳቀርብ አነሳስቶኛል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ጉቴሬዝ የሚደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት “ቀውሱን ለመፍታት እና ኢትዮጵያ ለቀጠናው መረጋጋት እንደገና የበኩሏን አስተዋፅዖ እንድታደርግ በኢትዮጵያውያን መካከል የእርስ በርስ ውይይት እንዲደረግ የሚያስችል ሊሆን ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሞቱበት እና በመቶ ሺዎች ለችግር የተጋለጡበት እንደሆነ የተመድ መረጃዎች ያመክታሉ።
ተመድ እና አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰሜን ትዮጵያ ው ግጭት የሚሳተፉ ሁሉም አካላት ወደ ተኩስ አቁም እንዲመጡ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸው የታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ እንደነበረ ይታወሳል።
ሆኖም ግን የህወሓት ሀይሎች የተናጠል የተኩስ አቁሙን ችላ በማለት ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች በከፈቱት ጥቃት በርካቶች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል።