አብረውት ፎቶ ለሚነሱ አድናቂዎቹ 121 ፓውንድ የሚያስከፍለው ፖለቲከኛ
የቀድሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ንግግር በሚያደርግበት አዳራሽ ለመታደም 160 ፓውንድ ክፍያ ግዴታ ሆኗል

ቦሪስ ጆንሰን ከቤተ መንግሥት ርቀው እየመሩት ያለው ህይወት ደብሯቸዋል ተብሏል
ቦሪስ ጆንሰን የብሪታንያው ወግ አጥባቂ ፖለቲከኛ ሲሆኑ ሀገራቸውን በጠቅላይ ሚንስትርነት መርተዋል።
የኮሮና ቫይረስ ህገ ደንቦችን ጥሰዋል በሚል በጫና ከስልጣን እንዲለቁ የተደረጉት ጆንሰን ዳግም ወደ ፖለቲካ የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ዋናውን ሚና የተጫወቱት ቦሪስ ጆንሰን ያላለቁ የፖለቲካ እቅዶቻቸውን ለማሳካት ዳግም ወደ ፖለቲካ ሊመለሱ እንደሚችሉ ቴሌግራፍ ጓደኞቻቸውን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የፊታችን መስከረም ወር ላይ በኤደንበርግ በሚዘጋጅ አንድ መድረክ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የቀረበላቸውን ግብዣ የተቀበሉት ጆንሰን አብሯቸው ፎቶ ለሚነሳ እና እጃቸውን ለሚጨብጣቸው ሰው እንደሚያስከፍሉ ተናግረዋል።
ወደ አዳራሹ ለመግባት ታዳሚዎች ከ53 ፓውንድ እስከ 160 ፓውንድ ክፍያ መክፈል ግዴታ ሲሆን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ፎቶ ለመነሳት ደግሞ 121 ፓውንድ ያስከፍላሉ ሲል ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
አሁን ላይ ለዴይሊ ሜይል በአምደኝነት እያገለገሉ ያሉት ቦሪስ ጆንሰን ከአሜሪካዊው ታዋቂ ጋዜጠኛ ተከር ካርልሰን ጋር ቃለ መጠይቅ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ አንድ ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ጆንሰን በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት በስምምነት እንዳይጠናቀቅ ትልቁን ሚና እንደተወጡ ቢገለጽም ጆንሰን እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ በይፋ ያሉት ነገር የለም።