አትሌት ለሜቻ ግርማ በፓሪስ የደረሰበት ጉዳት ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል አለመሆኑ ተገለፀ
የ3000 ሜትር የመሰናክል ውድድር ሲካሄድ ለአሸናፊነት የተጠበቀው ለሜቻ በመሰናክል ተጠልፎ ወድቆ ለደቂቃዎች ራሱን ስቶ ነበር
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች የአትሌቱን የጤና ሁኔታ እየተከተታለ መሆኑን አስታውቋል
አትሌት ለሜቻ ግርማ የደረሰበት ጉዳት ህይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል አለመሆኑ ተገለፀ።
አትሌቱ ትናንት ምሽት በስታድ ደ ፍራንስ የ3000 ሜትር መሰናክል ፍፃሜ ሲካሄድ በገጠመው አስደንጋጭ አደጋ ምክንያት ራሱን ስቶ ነበር።
ከወደቀበት በቃሬዛ ተነስቶ ወደ ሆስፒታል የተወሰደው አትሌት ለሜቻ፥ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ራሱን ማወቁና መነጋገር መጀመሩን ሲሆን አሰልጣኙ ለፈረንሳዩ ሌኪፕ ገልፀዋል።
በተደረጉለት ምርመራዎች በእግሩና በጭንቅላቱ ላይ ጉዳት እንዳልደረሰት መረጋገጡን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አስታውቋል።
የ23 አመቱ የርቀቱ ክብረወሰን ባለቤት በስታድ ደ ፍራንስ ለሀገሩ የወርቅ ሜዳልያ ለማስገኘት የመጨረሻውን ትንቅንቅ እያደረገ ባለበት ወቅት ነው በመሰናክል ተጠልፎ የወደቀው።
በቶኪዬ ኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ያገኘውና የሁለት ጊዜ የአለም ሻምፒዬናው የደረሰበት ጉዳት ለህይወቱ አስጊ ባይሆንም በሆስፒታል እንደሚቆይ ነው የተነገረው።
የፓሪስ ኦሎምፒክ አዘጋጆች አትሌት ለሜቻ በፍጥነት ከወደቀበት ተነስቶ ህክምና እንዲያገኝ አላደረጉም የሚሉ ወቀሳዎች ቀርቦባቸዋል።
አዘጋጆቹ ባወጡት መግለጫ ግን የህክምና ቡድን አባላት ወዲያውኑ አትሌቱን በማንሳት ተገቢውን እርዳታ ማድረጋቸውን በመግለፅ ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ እየተለዋወጥን ነው ብሏል።
በምሽቱ ውድድር ሞሮኳዊው የርቀቱ ንጉስ ሱፊያን ኤል ባካሊ አሸንፏል።
አሜሪካዊው ኬኔዝ ሮክስ እና ኬንያዊው አብራሃም ኪቢወት ደግሞ የብር እና የነሀስ ሜዳልያ አግኝተዋል።
ሱፊያን ኤል ባካሊ ከውድድሩ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ "በውድድሩ በአትሌቶች መካከል መከባበሩ ነበር፤ በኢትዮጵያዊው አትሌት ላይ በደረሰው ጉዳት አዝኛለው" ብሏል።
"ውድድሩን እስክጨርስ ድረስ የወደቀው አትሌት ማን እንደሆነ አላወቅኩም" የሚለውን አሜሪካዊው ኬኔዝ ሮክስ ጨምሮ በርካታ አትሌቶች ለሜቻ ግርማ በፍጥነት እንዲያገግም ተመኝተዋል።