ኢትዮጵያ ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን ገለጸች
ሳውዲ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ ግብጽ እና አልጀሪያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበዋል
በፈረንጆቹ 2009 የተመሰረተው ብሪክስ የብራዚል ፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ስብስብ ነው
ኢትዮጵያ ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን ገለጸች።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ጥቅሞቿን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መስራቷን ትቀጥላለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ተገልጿል።
ብሪክስ ከኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ እንደሚሰጠን እንጠብቃለን ያሉት አምባሳደር መለስ ከሌሎች ብሔራዊ ጥቅሞችን ሊያስጠብቁ ከሚችሉ ተቋማት ጋር መስራታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2009 የተመሰረተው ብሪክስ የፊታችን ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ ዓመታዊ ጉባኤውን እንደሚያደርግ አስታውቋል። በዚህ ጉባኤ ላይም ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ላቀረቡ ሀገራት ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
የፊታችን ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ ጉባኤውን እንደሚያደርግ የሚጠበቀው ብሪክስ አዳዲስ አባል ሀገራት ያቀረቡትን የእንቀላቀል ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
ሳውዲ አረቢያ፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ኢራን፣ ቱርክ፣ ግብጽ እና አልጀሪያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ዓለማችን በጥቂቶች ቁጥጥር ስር መዋል የለባትም የሚለው ይህ ጥምረት ተጨማሪ መገበያያ ገንዘብ ለዓለም እንደሚያስተዋውቅ ገልጿል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም በጦርነት እና ሌሎች ምክንያት የደረሱ መልካም ስምን ለማሻሻል የገጽታ ግንባታ ስራዎች በቀጣይ በስፋት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።
ለአብነትም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያሻሽሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎችን እንሰራለን ብለዋል።
112 አባላት ያለው የጅቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ተገልጿል።
በጦርነት እና ድርቅ ምክንያት ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን ይቀርብ የነበሩ እርዳታዎች መዘረፍን በሚመለከት ጉዳዩን ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ኮሚቴ በማጣራት ላይ መሆናቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።