በሰርጓ እለት ከስራ መሰናበቷን የሚገልጽ መልዕክት የደረሳት ብሪታንያዊቷ
ሙሽሪት በህይወቷ ትልቅ ቦታ የሰጠችውን እለት ወደሀዘን የለወጠ መልዕክት ከሃላፊዋ ተልኮላታል
በዋትስአፕ የተላከው መልዕክት ይዘትም መነጋገሪያ ሆኗል
ስራ ማግኘት ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ያለምንም ማስጠንቀቂያ የስንብት ደብዳቤ ሲደርስ ማስደንገጡ አያጠያይቅም።
ስንብቱ በሰርግ እለት ሲሆን ደግሞ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
ከወደ ብሪታንያ የተሰማው ዜናም በህይወት ዘመኗ ልዩ ቦታ ሰጥታ ስትጠባበቀው በነበረው እለት ከሃላፊዋ የስንብት መልዕክት በስልኳ እንደደረሳት ያሳያል።
አማንዳ የተባለችው እንስት አሳዛኙን ገጠመኝ ለታዋቂው ዩቲዩበር ቤን አስኪንስ አጋርታለች።
በቆጽሮስ የሰርግ ስነስርአቷን እያካሄደች የነበረችው አማንዳ ስልኬን ከጓደኞቼ ተቀብዬ የእንኳን ደስ ያለሽ መልዕክቶችን መመልከት እስክጀምር ድረስ ነገሮች ሰላማዊና አስደሳች ነበሩ ትላለች።
ሃላፊዬን ጨምሮ ባልደረቦቼ በእለቱ ሰርጌ መሆኑን ያውቃሉ የምትለው አማንዳ፥ ስልኳን ከጓደኞቿ ተቀብላ መልዕክቶችን ስትመለከት አስደንጋጩ ነገር መከሰቱን ተናግራለች።
“ሰርግሽ በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ መሆኑን እገምታለሁ፤ ጥሩ ጊዜ እመኝልሻለሁ” የሚለው መልዕክት፥ በመልካም ምኞት አልተጠናቀቀም።
“ከስራ እንድትሰናበች መወሰናችን ስነግርሽ እያዘንኩ ነው፤ የኢሜል አድራሻሽ ዝርዝር ጉዳዮችን ልኬልሻለሁ፤ በጣም አዝናለሁ መልካሙን ሁሉ እመኝልሻለሁ” ሲልም ይቀጥላል መልዕክቱ።
“መልዕክቱን ሳነብ ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ስልኬን ጥዬው ነበር፤ አረጋግተውኝ ኢሜሌን ስከፍትም የስራ ብቃቴ ለቦታው እንደማይመጥን ተመለከት” የምትለው አማንዳ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ እንዳልደረሳትም ትናገራለች።
በሰርጓ እለት በምትኳ የተቀጠረ ግለሰብ ስራ መጀመሩን መስማቷንም ነው የገለጸችው።
አሳዛኙን የስራ ስንብት አጋጣሚ የተመለከቱ ሰዎችም “አለቃዋ ምን አይነት ቂም ቢይዝና ምን በደልስ ብታደርስበት ነው በደስታዋ ቀን ይሄን ያደረገው?” የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
አዲሱን የህይወት ምዕራፍ ከባለቤቷ ጋር ከመጀመር ይልቅ በስራ ፍለጋ የተጠመደችው አማንዳ ከቀድሞ ሃላፊዋ ጋር ምንም አይነት ጸብ እንደሌላትና ጸብም ቢኖር በዚህ መልክ የሰው ልጅን ቅስም መስበር አስፈላጊ አለመሆኑን ተናግራለች።