የተከዜ ድልድይ መፍረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች አረጋገጡ
እንዳባጉናን እና ማይፀምሪ ከተሞችን የሚያገናኘው ድልድዩ መፍረስ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም
የድልድዩ መሰበር ሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ስራውን አስቸጋሪ ያደርገዋል- ዓለም አቀፍ ተቋማትየድልድዩ መሰበር ሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ስራውን አስቸጋሪ ያደርገዋል- ዓለም አቀፍ ተቋማት
እንዳባጉናን እና ማይፀምሪ (ልዮ ቀበሌ እምባማድሬ) ከተሞችን የሚያገናኘው የተከዜ ወንዝ ድልድይ መፍረሱን የአካባቢዎች ነዋሪ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ድልድዩ ዛሬ በመሰበሩ አሁን ላይ አገልግሎትእየሰጠ አይደለም።
ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ በይፋዊ የትዊተር ገጹ እንደጻፈው ድልድዩ መፍረሱን አረጋግጧል።
ድልድዩ እንዴት ? በማንና መቼ ጉዳት ደረሰበት? ስለሚለው ጉዳይ እስካሁን ምላሽ ከየትኛውም አካል ያልተገለጸ ሲሆን፤ ለድልድዩ መፍረስም ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።
ድልድዩ፤ ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ ወደ ትግራይ ሰብዓዊ ድጋፎች የሚገቡበት በር እንደነበርም ገልጿል።
ድልድዩ በመውደሙ በትግራይ ክልል በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት የሰብአዊ አርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ የማድረሱን ስራ እንደሚያስተጓጉለውም ነው የተጠቀሰው፡፡
በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የደቡብ እና ምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ የተከዜ ድልድይ ከጥቅም ውጭ መሆኑን ገልጾ የድልድዩ መሰበር ሰብዓዊ ድጋፍ የማድረስ ስራውን አስቸጋሪ ያደርገዋል ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሰኞ ዕለት የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል ለቆ እንዲወጣ እና በተናጠል ተኩስ እንዲቆም መወሰኑ ይታወሳል።