በነገው እለት ሁለተኛ ጨዋታውን የሚያደርገው ማንችስተር ዩናይትድ የቅድመ አሰላለፍ እና የተጫዋቾች ጉዳት ምን ይመስላል?
አዲሱ ፈራሚ ጆሽዋ ዚርክዚ ፣ ራሽፎርድ እና ካስሜሮ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ እንደሚካተቱ ይጠበቃል
ዩናይትድ በነገው አለት በአዲሱ የውድድር ዘመን ከሜዳው ውጭ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከብራይተን ጋር ያደርጋል
የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ በአዲሱ የውድድር ዘመን ሁለተኛ ጨዋታውን በነገው እለት ያደረጋል፡፡
ከሜዳው ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያደርገው ጨዋታ ከብራይተን ጋር የሚገናኘው ዩናይትድ በመጀመርያ ጨዋታ ያገኝውን አሸነፊነት ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
ባለፈው የውድድር ዘመን መጥፎ ጊዜ ያሳለፈው ቡድኑ በዘንድሮው አመት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ቡድኑን ለማጠናከር የተለያዩ ተጨዋቾችን በማስፈረም በዝውውር መስኮቱ ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሜዳው ፉልሀምን ባስተናገደበት ጨዋታ በጆሽዋ ዚርክዚ ብቸኛ ግብ በጠባብ ልዩነት ሲያሸንፍ፤ በአንጻሩ የነገ ተጋጣሚው ብራይተን ከኤቨርተን ጋር ያደረገውን ጨዋታ 3 ለምንም በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
ሜሰን ማውንትን በሁለተኛው አጋማሽ ቀይሮ የገባው ኔዘርላንዳዊው ጆሽዋ ዚርክዚ በ87ተኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ ዩናይትድን ከአቻ ውጤት ታድጋለች፡፡
በዘንድሮው የዝውውር መስኮት በ36.5 ሚሊየን ፓውንድ ዩናይትድን የተቀላቀለው ዚርክዚ ራስመስ ሆሉንድ ከጉዳት አለመመለሱን ተከትሎ በእርሱ ቦታ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ይካተታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታ በተቀያሪ ወንበር ላይ የነበረው አርጄንቲናዊው አሊሀንድሮ ጋርናቾ በዚህኛው ጨዋታም በተቀያሪ ወንበር ላይ ይገኛል፡፡ በእርሱ ቦታ በቅርቡ ከጉዳት ተምልሶ ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳየ የሚገኝው አማድ ዲያሎ ሊተካው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በግራ ተመላላሽ ቦታ ላይ ዲያጎ ዳሎት በቀኝ በኩል ደግሞ ኑሴየር ማዝራዊ የሚጫወቱ ሲሆን በተከላካይ ስፍራ ላይ ማቲያስ ዲላይት ሃሪ ማጉዋየርን በመተካት በመጀመርያው አሰላለፍ ላይ የሚኖር ይሆናል፡፡
በዚህም ሙሉ አሰላለፉ ኦናና ፣ ኑሴየር ማዝራዊ ፣ ሜይኖ ፣ ዲላይት ፣ ማርቲኔዝ ፣ ዳሎት ፣ ካስሜሮ ፣ አማድ ፣ ፈርናንዴዝ ፣ ራሽፎርድ እና ዚርክዚ ሊካተቱ እንደሚችል የእንግሊዝ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡
በነገው እለት ማንችስተር ሲቲ ከኢፕስዊች ፣ አርሰናል ከአስቶንቪላ ፣ ቶትንሀም ከኤቨርተን ፣ ክርስቲያል ፓላስ ከዌስትሀም ፣ ፉልሀም ከሌስተር ሲቲ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት 8 ቡድኖች በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ይገኛሉ፡፡