ዩክሬን በሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት የበርካታ ሀገራት ቅጥረኛ ወታደሮችን አሰማርታለች
ብሪታንያዊው ለዩክሬን ሲዋጋ በሩሲያ ጦር ተማረከ።
ከሶስት ዓመት በፊት የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መልኩን እየቀያየረ እንደቀጠለ ይገኛል።
ዩክሬን ቁልፍ የሎጅስቲክስ ማዕከል የሆነችው ፐሮቭስካ ከተማን በሩሲያ እንዳትያዝ በሚል በድንገት ሳይታሰብ ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት ጥቃት ከፍታ ነበር፡፡
ባሳለፍነው ነሀሴ ላይ በተጀመረው የኩርስክ ግዛት ጦርነት ዩክሬን ከ 1 ሺህ 200 ስኩዌር ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው አካባቢን ተቆጣጥራለች፡፡
ዩክሬን የኩርስኩን ጥቃት የከፈተችው በምስራቅ ዩክሬን በኩል እየገሰገሰ የነበረውን የሩሲያ ጥቃት ለመግታት በማሰብ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ይሁንና ሩሲያ እንደታሰበው በምስራቅ ዩክሬን በኩል የሰማራችውን ጦር ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ከማድረግ ይልቅ ወደ ፊት እንዲገፋ አድርጋለች፡፡
በዚህ የሩሲያ መልሶ ማጥቃት የበርካታ ሀገራት ቅጥረኛ ወታደሮችን እንደተገደሉ የሩሲያ መከላከያ ባወጣው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
በዚህ ዘመቻ የብሪታንያ ጦር የቀድሞ አባል በሩሲያ ጦር መማረኩን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የተማረከው ወታደር ስኮት አንደርሰን እንደሚባል የተገለጸ ሲሆን በፖላንድ በኩል አድርጎ ወደ ዩክሬን እንደገባ ተናግሯል።
ሩሲያ ከዚህ በፊትም የብሪታንያ እና ሌሎች ሀገራት ቅጥረኛ ወታደሮችን በውጊያ ወቅት ማርካ የነበረ ሲሆን በድርድር የተወሰኑት ተለቀዋል።
ሩሲያ ወደ ኩርስክ የገባውን የዩክሬን ወታደሮችን ለማስወጣት 50 ሺህ ወታደሮችን አሰማርታለች የተባለ ሲሆን 11 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችም በስፍራው እንደሰፈሩ የዩክሬን ጦር አዛዦች በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል።