ብሪታንያ ለመከላከያ ሰራዊቷ የኤሌክትሪክ መኪኖችን መጠቀም ልትጀምር ነው
ወታደራዊ ተቋማት የኤሌክትሪክ መኪኖችን ከአዋጭነት አንጻር እየተጠቀሙ አይደለም

የኤሌክትሪክ መኪኖች ለወታደራዊ ተቋማት ጥቅም ላይ የማይውሉት ለጥቃት ያጋልጣሉ በሚል ነው
ብሪታንያ ለመከላከያ ሰራዊቷ የኤሌክትሪክ መኪኖችን መጠቀም ልትጀምር ነው።
የብሪታንያ ጦር የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለመጠቀም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ሀገሪቱ በ2025 የኤሌክትሪክ መኪኖችን በሙከራ ደረጃ መጠቀም እንደሚጀምር አስታውቋል።
እንደ ዴይሊ ኤክስፕረስ ዘገባ ከሆነ ብሪታንያ የኤሌክትሪክ መኪኖች ለወታደራዊ አገልግሎቶች መጠቀም እጀምራለሁ ብሏል።
ወታደራዊ ተቋማት ከውጤታማነት አንጻር እና አደጋዎችን ከመቀነስ አንጻር በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን በመጠቀም ይታወቃሉ።
ይሁንና አሁን ላይ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች እንዲቀሩ ሀገራት ፖሊሲዎችን እየቀረጹ ሲሆን ብሪታንያም ቀስ በቀስ ጦሯን የኤሌክትሪክ መኪኖችን እንዲጠቀሙ ማቀዷን አስታውቃለች።
ሀገሪቱ በ400 ሺህ ፓውንድ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለመግዛት በጀት እንደያዘች የገለጸች ሲሆን ባለሙያዎች ግን የመንግስታቸውን እቅድ ተችተዋል።
ከቀድሞው የብሪታንያ ጦር አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ኮለኔል ሪቻርድ ኬምፕ እንዳሉት የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመጠቀም የሚደረጉ ወታደራዊ ተልዕኮዎች እክል ሊገጥማቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
ሌላኛው የብሪታንያ የቀድሞ ወታደራዊ አዛዥ ኮለኔል ቲም ኮሊንስ የኤሌክትሪክ መኪኖች ወታደራዊ ተልዕኮዎችን መፈጸም የሚያስችል አቅም አይኖራቸውም ብለዋል።
"ወታደራዊ ተልዕኮዎች ለፋሽን ተብለው የሚደረጉ አይደሉም" ሲሉም እኝህ የቀድሞ አዛዥ ለቴሌግራፍ ተናግረዋል ።
የብሪታንያ መከላከያ ቃል አቀባይ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኖሎጂ ለወታደራዊ ተቋማትም የራሳቸውን እድል ይዘው እንደመጡ አስታውቋል።
በ2025 በሚደረገው ሙከራ የኤሌክትሪክ መኪኖች ለወታደራዊ ተልዕኮዎች መሳካት የሚኖራቸው ሚና ይገመገማል ሲልም ሚንስቴሩ ገልጻል።