የእንግሊዝ ንጉሳውያን ቤተሰብ የሰሴክሱ ልዑል ሃሪና ባለቤቱ ሜጋን ስለዘረኝነት ባወሩት ጉዳይ ላይ ምላሽ ሰጠ
ሜጋን "በህይወት መቆየት አስጠልቷት" እንደነበር ይፋ አድርጋለች
መግለጫው "መላው ቤተሰቡ ለሃሪና ሜጋን ያለፉት ዓመታት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበሩ ሲያውቅ አዝኗል" ብሏል
የሰሴክሱ ልዑል ሃሪና ባለቤቱ ሜጋን ከኦፕራ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ወቅት የተነሳውን ዘረኝነትን የተመለከተ አስተያየት የባኪንግሃም ቤተመንግሥት "አሳሳቢ" እና "በአንክሮ የምንከታተለው ጉዳይ" ነው በማለት ምላሽ ሰጠ።
ከቤተመንግሥቱ የወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው "በጥንዶቹ የተነሱና ከዘረኝነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች" በተለየ ሁኔታ እንመለከተዋለን ሲል ገልጿል። "መላው ቤተሰቡ ለሃሪና ሜጋን ያለፉት ዓመታት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበሩ ሲያውቅ አዝኗል" ሲልም ነው መግለጫው ያስታወቀው፡፡ "የሚባሉት ነገሮች ሊለያዩ ይችላሉ" ነገር ግን ጉዳዩን በተለየ ሁኔታ እንመለከተዋለን ሲልም የቤተ መንግስቱ መግለጫ አመልክቷል፡፡
ንጉሣውያን ቤተሰቦች ይህንን ጉዳይ የቤተሰብ እንደሆነ እና በግል ውይይት እንዲደረግበት መፈለጋቸውና ለዚህም ስብሰባ መቀመጣቸው ተሰምቷል። ቤተመንግሥቱ ሃሪናና ባለቤቱ ሜጋን "ሁሌም የሚወደዱ የቤተሰብ አባላቶች ናቸው"ም ብሏል። ሜጋን ከኦፕራ ጋር በነበራት ቃለ ምልልስ ወቅት የልጇ የአርቺ የቆዳ ቀለምን በሚመለከት የንጉሣውያን ቤተሰብ አባል ባለቤቷን ሃሪን መጠየቁንም ገልፃለች፡፡
ጉዳዩ በዚህ ብቻ አላበቃም የምትለው ተዋናይት ሜጋን መርክል በተነሳው የዘረኝነት ጉዳይ ምክንያት ልጇ አርቺ ሳይቀር በቆዳው ቀለም ብቻ የልዑልነት መአረግ ሳያገን ተነፍጎ እንደቆየ ተናግራለች፡፡ ሜጋን አክላ በእንግሊዝ የንጉሣውያን ቤተሰብ ውስጥ የነበራት ህይወት ከመክፋቱ የተነሳ "በህይወት መቆየት አስጠልቷት" እንደነበር ይፋ አድርጋለች።