አሜሪካና ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ጉዳይ ለመምከር በሳኡዲ አረቢያ ሊገናኙ ነው
የኃይትሀውስ የዩክሬን መልእክተኛ የንግግሩ አላማ ትራምፕ፣ የየሩሲያው ፑቲንና የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ተገናኝተው እንዲነጋገሩ ለማመቻቸት ነው ብለዋል

ሶስት አመት ገደማ የሆነው ጦርነት ሲቀጥል ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ቀስበቀስ በርካታ መንደሮችን መቆጣጠሯን ቀጥላለች
አሜሪካና ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት ጉዳይ ለመምከር በሳኡዲ አረቢያ ሊገናኙ ነው ተባለ።
የአሜሪካና ሩሲያ ባለስልጣናት ሶስት አመት ገዳማ ያስቆጠረውን የዩክሬይን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ንግግር ለመጀመር በቀጣዮቹ ቀናት በሳኡዲ አረቢያ ሊገናኙ መሆናቸውን ሮይተርስ ስለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።
ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝደንት ዲጄ ቫንስ ጋር ባለፈው አርብ እለት በጀርመን የተገናኙት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ዩክሬን በሳኡዲ አረቢያ በሚካሄደው ንግግር አለመጋበዟንና ኪቭ ከስትራቴጂክ አጋሮቿ ጋር ሳትነጋገር ከሩሲያ ጋር ንግግር እንደማትጀምር ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልዝና የኃይት ሀውስ የመካከለኛው ምስራቅ መልእክተኛ ስቴቭ ዊትኮፍ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እንደሚጓዙ የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ሚካኤል ማኩል መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ባለስልጣናቱ ከሩሲያ በኩል ማንን እንደሚያገኙ ግልጽ አልተደረገም ተብሏል።
ማኩል ከሙኒክ የደህንነት ስብሰባ ጎን ለጎን እንደተናገሩት የንግግሩ አላማ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንና የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ተገናኝተው እንዲነጋገሩ በማመቻቸት ሰላም እንዲሰፍንና ጦርነቱ እንዲቆም ማድረግ ነው።
ባለፈው ጥር ወር ወደ ኃይትሀውስ የገቡት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት በፍጥነት ለማስቆም ቃል ገብተዋል። ትራምፕ ከፑቲንና ዘለንስኪ ጋር የተናጠል ንግግር ማድረጋቸው የዋሽንግተን የአውሮፓ አጋሮች ከሰላም ንግግሩ ሂደት እንገለላን የሚል ስጋት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።
ይህ የአውሮፓውያን ስጋት የትራምፕ የዩክሬኑ መልእክተኛ አውሮፓውያን በንግግሩ ቦታ እንደሌላቸው ከገለጹ በኋላ በሰፊው ተረጋግጧል። ቅዳሜ ጠዋት ሩቢዮ ከሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስርጌ ላቭሮቭ ጋር የስልክ ንግግር አድርገዋል። ሚንስትሮቹ በፕሬዝደንት ትራምፕና ፑቲን መካከል ስብሰባ ለማመቻቸት በየጊዜው ለመነጋገር መስማማታቸውን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ፕሬዝደንት ዘለንስኪ አረብ ኢምሬትስን፣ሳኡዲ አረቢያንና ቱርክን በቅርቡ እንደሚጎበኙ የገለጹ ቢገልጹም የአሜሪካ ወይም የሩሲያን ባለስልጣናት ለማግኘት እቅድ ስለመያዛቸው ግልጽ አላደረጉም።
ሶስት አመት ገደማ የሆነው ጦርነት ሲቀጥል ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ቀስበቀስ በርካታ መንደሮችን መቆጣጠሯን ቀጥላለች።
ሩሲያ ዩክሬን የኔቶ አባል የመሆን ጥያቄዋን እንድታነሳና አዲስ የመሬት ይዞታ ሁኔታዎችን እንድትቀበል የምትፈልግ ሲሆን ዩክሬን ይህን እንደማትቀበል በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል።