ቦሪስ ጆንሰን የፓርቲያቸውን የመተማመኛ ድምጽ ካላገኙ ከፓርቲም ከመንግስትም ኃላፊነት ይነሳሉ ተብሏል
በብሪታኒው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ላይ የመተማመኛ ድምጽ ሊሰጥ መሆኑን ገዥው ኮንዘርቫቲቭ (ወግ አጥባቂው) ፓርቲ አስታወቀ፡፡
የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ የፈለጉት በፓርቲው ውስጥ ያሉት ሕግ አውጭ አባላት መሆናቸው ተገልጿል፡፡ 15 በመቶ የሚሆኑ የሕግ አውጭ አባላቱ በሊቀመንበራቸው ደስተኛ ባለመሆናቸው የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ መጠየቃቸው ነው የተነገረው፡፡
አባላቱ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ተጥለው የነበሩ ህግጋትን በጣሱት በቦሪስ ጆንሰን አመራር ላይ መተማመን ተስኖናል ማለታቸውን ተከትሎ ነው ድምጽ የሚሰጡት፡፡
ቴሬዛ ሜይን በመተካት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ጆንሰን ዛሬ የመተማመኛ ድምጽ ከተሰጠባቸው በኋላ የፓርቲው ሊቀ መንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መቀጠል አለመቀጠላቸው ይወሰናል ተብሏል፡፡
የወሲብ ቪዲዮዎችን በስልካቸው መመልከታቸውን ያመኑት የብሪታኒያ ፓርላማ አባል ከስልጣን ታገዱ
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የመተማመኛ ድምጽ የሚሰጡት 359 የኮንዘርቫቲቭ (ወግ አጥባቂ) ፓርቲ የህግ አውጭ አባላት ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግስት እና በፓርቲ ኃላፊነት ለመቀጠል የ180 የፓርቲውን ሕግ አውጭ አባላት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
የቀድሞው ጋዜጠኛ ቦሪስ ጆንሰን ይህንን የመተማመኛ ድምጽ ካላገኙ በፓርቲው ሊቀ መንበርነት የማይቀጥሉ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ፓርቲው የድጋፍ ድምጽን ካጡ በቦሪስ ጆንሰን ምትክ አዲስ ሊቀመንበር ሊመርጥ እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
ሊመረጥ የሚችለው አዲስ የፓርቲው ሊቀመንበርም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ይሁንና ቦሪስ ጆንሰን የመተማመኛ ድምጽ የሚያገኙ ከሆነ የስልጣን ዘመናቸውን መጨረስ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ቦሪስ ጆንሰን፤ ጋዜጠኛ፣ የለንደን ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ማገልገላቸው ይታወሳል፡፡ ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት ለመውጣት (ብሪኤግዚት) መወሰኗን ተከትሎ የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ከኃላፊነት በመልቀቃቸው ቦሪስ ጆንሰን ሃላፊነቱን መረከባቸው ይታወሳል፡፡