ሚኒስትሩ ከስራ የታገዱት ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል በሚል ነው
የብሪታንያው የንግድ ሚኒስትር ኮነር በርንስ ከስራ ታገዱ፡፡
ከአንድ ወር በፊት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ሊዝ ትሩስ የንግድ ሚኒስትሩን ኮነር በርንስን ከስራ ማገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከስራ የታገዱት የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ የሖነው ወግ አጥባቂ ፓርቲ ላለፉት ሶስት ቀናት ባካሄደው ጉባኤ ላይ ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል በሚል እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቦርንማውዝን ወክለው የብሪታንያ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባል የሖኑት በርንስ ከወግ አጥባቂ ፓርቲ ስብሰባ እና ከመንግስታዊ ስራ የታገዱ ሲሆን ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸውም ተወስኗል ተብሏል፡፡
ከስራ የታገዱት ኮነር በርንስ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሉት በብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በወግ አጥባቂ ፓርቲ የደረሳቸው ክስ እንደሌለ ገልጸው በቀጣይ የተነሳባቸውን ክስ እና መልካም ስማቸውን ለማስጠበቅ ከህግ አካላት ጋር ትብብር እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
የ50 ዓመቱ የብሪታንያ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባሉ በርንስ የቀደሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የቅርብ ጓደኛ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
በርንስ ከሁለት ዓመት በፊት ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ተመሳሳይ ያልተገባ ድርጊት ፈጽመዋል የሚል ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸው የነበረ ሲሆን ክሱን ተከትሎም ከንግድ ሚኒስትርነታቸው በራሳቸው ፈቃድ ስልጣን ለቀው ነበር፡፡
አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስ ከአንድ ወር በፊት ወደ ስልጣን ሲመጡ ኮነር በርንስን ድጋሜ የንግድ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብሪታንያ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ያልተገቡ ድርጊቶችን በመፈጸም ክሶች እየቀረቡባቸው ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ሁለት ባለስልጣናት ስልጣናቸውን በራሳቸው ፍላጎት ለቀዋል፡፡