“መንግስት ለዜጎች ያቀረበው ጥሪ፤ ሀገርን ከብተና ለመታደግ ነው”- የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም “የህወሃት እና ሸኔ ጋብቻ አዲስ ነገር አይደለም“ ብለዋል
የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ከትናንት በስቲያ ሀገር አቀፍ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል
መንግስት ኢትዮጵያውያን ሀገርን ከብተና እንዲታደጉ ጥሪ ማቅረቡን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ ከትናንት በስቲያ መንግስት ያወጣው መግለጫ ዜጎች ሀገራቸውን ከብተናና ከመፍረስ እንዲታደጉ ጥሪ ያስተላለፈበት መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ሀገር አቀፍ ጥሪ ያቀረበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጀው ህወሃት በአማራ እና በአፋር ብሔራዊ ክልሎች ላይ ወረራ ማካሄዱን ተከትሎ መሆኑንም ቢለኔ ስዩም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጀው ህወሃትን ወረራ በማንኛውም መንገድ ለመከላከል መገደዳቸውንም ነው ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ያስታወቁት።
ከትናንትና ወዲያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተላለፈው ጥሪ በሀገር ቤትም በውጭም የሚገኙ ዜጎች ህወሃት ሀገርን ለማፍረስ እና ለመበተን የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀለብሱና ሀገርን እንዲታደጉ መሆኑን ያነሱት ቢለኔ ስዩም፤ ዜጎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት፤ ልዩ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች እንዲቀላቀሉም ጥሪ መተላለፉን ተናግረዋል።
አቅማቸው የፈቀደ ሁሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን፤ ልዩ ኃይሎችን እና ሚሊሻዎችን ከመቀላቀልም ባለፈም “የህወሃትን የጥፋት ድርጊት” እንዲቀለብሱም መንግስት ትዕዛዝ ማስተላለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል።
ኢትዮጵያውያን የመከላከያ ሰራዊትን እና ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች በመቀላቀል፤ ከተሞቻቸውንና አካባቢያቸውን እንዲሁም ሕዝባቸውን እንዲጠብቁም ጥሪ መተላፉን ፕሬስ ሴክሬታዋ ተናግረዋል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን “የህወሃትን የጥፋት ድርጊት” ለዓለም እንዲያጋልጡ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉም ጥሪ መቅረቡን ቢለኔ ስዩም አስታውቀዋል።
ህወሃት እና “ኦነግ ሸኔ“
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀውና መንግስት “ኦነግ ሸኔ“ ብሎ የሚጠራው እና ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት“ ብሎ የሚጠራው ድርጅት መሪ እንደሆነ የሚነገረው ኩምሳ ድሪባ ከህወሃት ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት መደረሱን ትናንት ለአሶሺትድ ፕሬስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህንን ተከትሎ ጥያቄ የቀረበላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጅታል ሚዲያ ኃላፊ ቢለኔ ስዩም "ህወሃትና ሽኔ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በጋራ ሲሰሩ የቆዩ የሽብር ቡድኖች ናቸው" ሲሉ መልሰዋል፡፡ አብሮ ለመስራት መስማማታቸውንም አዲስ ነገር እንዳልሆነ እና ቀድሞ የሚታወቅ መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡
ቢለኔ ስዩም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው የህወሃት ቡድን በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሸኔን በመጠቀም የሽብር ስራውን ሲያከናወን መቆየቱን አስታውቀዋል።
መንግስት ቡድኖቹን በአሸባሪነት የፈረጃቸው ሀገር ለማፍረስ በጋራ እየሰሩ መሆኑን በተጨባጭ መረጃ በማግኘቱ መሆኑንም ቢለኔ ስዩም ገልጸዋል።
ህወሃት ኢትዮጵያን ሲመራ በቆየባቸው ጊዜያት የኦሮሞን ወጣቶች "ኦነግ ናችሁ" በሚል አሰቃቂ ግድያ፣ ድብደባና ግፍ ሲፈጽም መቆየቱን ያነሱት ቢለኔ ስዩም፤ የሁለቱን ቡድኖች የሰሞኑ ጉዳይ ለዘመናት ለኦሮሞ ህዝብ መብት ሲታገሉ በቆዩት አንጋፋ የፖለቲካ ልሂቆች ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረውም አንስተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መንግስት ሀገረመንግስቱን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ላይ ተሳትፏል ያለውን ህወሓትን በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስትና ትግራይን ክልል ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ግጭት ከተጀመረ ከ8 ወር በኋላ የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት ሰራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው የትግራይን ቀውስ በውይይት ለመፍታት በማቀዱ መሆኑን ቢገልጽም ግጭቱ አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፏፍቷል።
ጥቅምት 24፣2013 በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎችም የተስፋፋ ተስፋፍቷል። መከላከያ ሰራዊትና የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ አካላት የህወሓትን እንቅስቃሴ ለመግታት ጥቃት መክፈታቸውም መንግስት አስታውቋል።