![](https://cdn.al-ain.com/images/2022/1/24/252-123024-whatsapp-image-2022-01-24-at-11.17.04_700x400.jpeg)
በምዕራብ አፍሪካ በአንድ ዓመት ውስጥ መፈንቅለ መንግስት በሶስት አገራት ላይ ተፈጽሟል
የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት በሀገሪቱ ወታደሮች መታሰራቸው ተነግሯል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኡጋዱጉ ውስጥ በወታደሮች ታስረው ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ካቦሬ የታሰሩት በአማጺ ወታደሮች ሲሆን፤ በሀገሪቱ መዲና ኡጋዱጉ ባለ አንድ ወታደራዊ ማዘዣ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የቡርኪና ፋሶ መንግስት በትናንትናው ዕለት የወታደሮቹ እንቅስቃሴ መፈንቅለ መንግስት አለመሆኑን ገልጾ ነበር።
በቡርኪና ፋሶ ወታደሮች ውስጥ ጥያቄ እንዳነሱ የሚነገርላቸው አማጺ ወታደሮች አዛዦቻቸውን ጨምሮ መሪዎችን ገድለዋል።
ይሄንን ተከትሎም የቡርኪና ፋሶ መንግስት ከትናንት ምሽት ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ የሰዓት ገደብ ጥሎም ነበር፡፡
በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መፈንቅለ መንግስት ማድረግ የተለመደ ሲሆን አሁን ደግሞ ተራው የቡርኪና ፋሶ ሆኗል።
የማሊ ወታደሮች በኮለኔል አስሚ ጎይታ የተመራ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ አሁን ላይ የሽግግር ጊዜያዊ መንግስት መስርተው ማሊን በማስተዳደር ላይ ይገኛል።
ኢኳቶሪያል ጊኒም ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ የሀገሪቱን ሲቪል አስተዳድር በማስወገድ ወታደረዊ መንግስት የመሰረተ ሲሆን እነዚህ ወታደራዊ መሪዎች ስልጣናቸውን በህዝብ ለተመረጡ መንግስታት እንዲያስረክቡ ኢኮዋስን ጨምሮ አፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ተቋማት በማሳሰብ ላይ ናቸው።