የቡርኪና ፋሶ የጦር መኮንኖች በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ወታደራዊ መንግስት መፍረሱን አስታወቁ
ኢኮዋስ ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ስልጣን ለመውሰድም ሆነ ለማስቀጠል የሚደረግ ጥረት እቃወማለሁ ብሏል
ሌ/ኮሎኔል ዳምቢባ ከመሪነት የተወገዱት በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱትን እስላማዊ አማጺያንን መቆጣጠር ስላልቻሉ ነው ተብሏል
የቡርኪና ፋሶ የጦር መኮንኖች በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ የነበረውን የፖል ሄንሪ ዳምቢባ ወታደራዊ መንግስት መፍረሱ አስታወቁ፡፡
የጦር መኮንኖቹ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ጭንብል በለበሱ ወታደሮች ታጅበው በሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው እንደተናገሩት የወታደራዊ መንግስት መሪው ሌትናል ኮሎኔል ዳምቢባ ከመሪነት የተወገዱት፣ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱትን እስላማዊ አማጺያንን በአግባቡ መቆጣጠር ስላልቻሉ ነው ብለዋል፡፡
“እየተባባሰ የሚሄድ ችግር በገጠመን ጊዜ ዳምቢባ በደኅንነት ጉዳዮች (ጦሩን በአዲስ መልክ ማደራጀት) ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ በተደጋጋሚ ሞክረናል፤ ነገር ግን የዳምቢባ ተግባር ለማድረግ ካቀድነው ውጪ በመሆኑ አሁን ከስልጣን እንዲወገድ ወስነናል” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
መኮንኑ ጨምረውም ላልተወሰነ ጊዜ ሁሉም የሀገሪቱ ድንበሮች ዝግ እንደሚሆኑ እና የትኛውም አይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መከልከሉ፣ ህገ መንግስት መታገዱንና የሌሊት የሰዓት እላፊ መታወጁ አሳውቀዋል።
አዲሱ መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ የሌትናል ኮሎኔል ዳሚባ ሁኔታን በተመለከተ ያሉት ነገር እንደሌለም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ብሔራዊ ባለድርሻ አካላት አዲስ የሽግግር ቻርተር እንዲያጸድቁ እና አዲስ ሲቪል ወይም ወታደራዊ ፕሬዝዳንት እንዲሾሙ በቅርቡ እንደሚጋብዙም ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ህዝቦች በዲሞክራሲያዊ መንገድ ከተመረጡት የቀድሞ መሪዎች የበለጠ ታጣቂዎችን በመቆጣጠር ረገድ ስኬታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ ወታደራዊ ጁንታዎችን በደስታ ተቀብለዋል።
ቡርኪና ፋሶ በጎረቤት ማሊ የጀመረው እና ከሰሃራ በረሃ በስተደቡብ ወደ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የተዛመተው ከአልቃይዳ እና እስላማዊ መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች የሚፈጽሙት የጥቃት ማዕከል እንደሆነች መምጣቷ ይነገራል፡፡
ያም ሆኖ በትናንትናው እለት የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት በቀጣነው ሲቪል መንግስታት እንዲኖሩ እየታተረ ላለው የምዕራብ አፍሪካው የኢኮኖሚ ማህበረሰብ /ኢኮዋስ/ ሌላ የቤት ስራ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
የሌ/ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳምቢባ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ መግለጫ ያወጣው ኢኮዋስ ፤ ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ስልጣን ለመውሰድም ሆነ ለማስቀጠል የሚደረግ ጥረት እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡
"ከሃምሌ 1 ቀን 2024 በፊት ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ እንዲመለስ ከሽግግር ባለስልጣናት ጋር የተደረሰው ስምምነትና የጊዜ ሰሌዳ እንዲከበር " ሲልም ጠይቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ቡርኪናፋሶ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ነገር “በእጅጉ እንዳሳሰባት” የገለጸችው አሜሪካ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ዜጎቿ እንቅስቃሴያቸውን እንዲቆጥቡ መክራለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ “መረጋጋት እንዲሰፍንና ሁሉም ወገኖች ከየትኛውም ድርጊት እንዲቆጠቡ” ጥሪ አቅርበዋል።