አሜሪካ ለቡርኪናፋሶ ልትሰጥ የነበረውን የ160 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አቆመች
የአሜሪካ ዕርዳታን የማቆም ውሳኔ “በቡረኪናፋሶ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ተከትሎ የመጣ” እንደሆነም ተመላክቷል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፡ አሜሪካ በጤናው ዘርፍ ቡርኪናፋሶን ለመርዳት እያጤነች መሆኑንም አስታውቋል
አሜሪካ ለቡርኪናፋሶ ልትሰጥ የነበረውን 160 ሚሊዮን ዶላር ገዳማ የሚሆን ዕርዳታ አቆመች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ከሆነ፤ አሜሪካው እርዳታውን ያቆመችው እንደፈረንጆቹ ከ2105 አንስቶ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ይመሩ የነበሩትን ሮክ ካቦሬ በጥር ወር በተካሄደ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የተሳካ መፈንቅለ መንግስት የመሩት የቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መሪ ፖል ሄንሪ ዳሚባ ከሳምንታት በኋላ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው “ጥንቃቄ የተመላበት ግምገማ” ካካሄደና ነገሮችን በሚገባ ካጤነ በኋላ ነውም ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
ቃል አቀባዩ አክለው ውሳኔው የተላለፈው ፤ የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ ዲሞክራሲን ለማስፈን ከሚደረገው ገንዘብ በስተቀር የተመረጠን የመንግስት መሪ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከተወገደ ወይም ወታደራዊ ኃይሉ ወሳኝ ሚና የሚጫወትብት ሁኔታ ከተፈጠረ መቆም አለበት በሚለው የአሜሪካ ህግ መሰረት እንደሆነም አስረድቷል።
በዚህም የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በቡርኪናፋሶ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እንደተፈፀመ በመገምግም ለቡርኪናፋሶን መንግስት ሊሰጥ የነበረውን ወደ 158.6 ሚሊዮን ዶላር የውጭ እርዳታ ገድቧል ነው ያሉት ኔድ ፕራይስ፡፡
ይሁን እንጅ በጤናው ዘርፍ የነፍስ አድን ዕርዳታዎችን ለማቅረብ የሚቻልበትን ሁኔታ ላይ እየተመከረ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ለኮንግረስ በላከው ማሳሰቢያ ተመላክቷል፡፡
አሜሪካ፡ የሀገሪቱ ወታደራዊ መሪ ፖል-ሄንሪ ዳሚባ በጥር 24 ቀን ካቦሬን ከስልጣን ካስወገደ በኋላ ለቡርኪናፋሶ በአምስት አመታት ውስጥ ለግብርና እና ውሃ ልማት ድጋፍ የሚውል የ450 ሚልዮን እርዳታ ለማቆም እንደምትገደድ ባለፈው ጥር 31/2022 ማስጠንቀቋ የሚታወስ ነው፡፡
ነገር ግን ዋሽንግተን በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር የተከሰቱት ድርጊቶች መፈንቅለ መንግስት መሆናቸውን ለማጣራት እና በእርዳታው እጣ ፈንታ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ እስካሁን ቆይታለች፡፡
ደሚባ ሮክ ካቦሬን ከስልጣን ያስወገደው ካቦሬ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለውን እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ያስገደደውን የእስልምና አማፂ ቡድን መግታት አልቻሉም በሚል ምክንያት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ደሚባ ለምን ያህል ጊዜ ስልጣን ለመያዝ እንዳሰቡ የታወቀ ነገር ባይኖርም ለቀጣናው ኅብረት ከምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ወደ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲመለሱ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በቡርኪናፋሶ የተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በፈረንጆቹ ከ2020 ጀምሮ በማሊ፣ ጊኒ እና ቻድ የተካሄደውን ተከትሎ ሲሆን በቀጠናው መሪዎች መካከል መፈንቅለ መንግስቱ ይስፋፋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።