“የውክልና ጦርነት ለማንም ስለማይጠቅም በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አንገባም”- የሱዳኑ አምባሳዳር
የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት በመንግስታት መካከል በሚፈጠሩ አጀንዳዎች የማይለወጥ መሆኑንም አስታውቀዋል
አምባሳደር ጀማል አል ሼክ የኢትዮጵያ መንግስት ብሄራዊ ውይይት ለማካሄድ እያሳየ ያለው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው ብለዋል
ሱዳን በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ጀማል አል ሼክ ተናገሩ።
አምባሳደሩ የይህንን ያሉት ኢትዮ-ሱዳን ግንኙነትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በማስመልከት ከአል-ዐይን ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ነው።
አምባሳደር ጀማል ኢትዮጵያ እና ሱዳን ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ግንኙነቱ ከዲፕሎማሲ በዘለለ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትም ጭምር የጎለበተ በመሆኑ፤ የአሁኑን ጨምሮ በተለያዩ ወቅቶች “በመንግስታት መካከል በሚፈጠሩ አጀንዳዎች የማይለወጥ ነው” ሲሉም፤ የሀገራቱ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑንም አምባሳደሩ ያስረዳሉ።
ሱዳን የኢትዮጵያን መረጋጋት እና ሰላም የምትመኝ ታሪካዊ ወዳጅ ሀገር መሆኗንም አምባሳደር ጀማል ለአል ዐይን ተናግረዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ፤ ሱዳን ህወሃትን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚዎችን ትረዳላች የሚሉ ክሶች በኢትዮጵያ በኩል ይቀርብላችኋል በሚል ከአል-ዐይን ኒውስ ለቀረበላቸው ጥያቅም አምባሳሳሩ ተከታዩን ምለሽ ሰጥተዋል።
“አዎ ፤ ሱዳን ህወሃትን ጨምሮ ሌሎች ቡድኖች ታገግዛለች የሚሉ ክሶች እንሰማለን፤ ማረጋገጥ የምፈልገው ነገር ቢኖር ግን ይህ የእኛ ስትራቴጂ፣ ፖሊሲ እና አቋም አይደለም፤ ሱዳን በየትኛውም ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም፤ ምክንያቱም የውክልና ጦርነት ለማንም እንደማይጠቅም እንረዳለን፤ ይህ ደሞ ለእኛ እንደ አማራጭ ሊሆን አይችልም” ነው ያሉት አምባሳደሩ።
አምባሳደሩ “የእኛ ፍላጎት በኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ተረጋግጦ ማየት እንዲሁም ረዥም ዘመናት ያስቆጠረውን የሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ከፍተኛ ደራጃ ማሸጋገርና መተባበር ነው” ሲሉም አክለዋል።
“አሁን በኢትዮጵያ ያጋጠሙ የውስጥ ችግሮች ሁሉ መፍትሄ እንደሚያገኙም ምኞታችን ነው” ያሉት አምባሳደር ጀማል፤ የኢትዮጵያ መንግስት ብሄራዊ ውይይት ለማካሄድ እያሳየ ያለን ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
“ውይይቱ ተሳክቶ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንደሚያመጣም ምኞታችን ነው” ሲሉም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል