ሞስኮ በአፍሪካ ፖለቲካና ምጣኔ-ሀብት ተጽዕኖ ለመፍጠር ጥረት እያደረገች ነው ተብሏል
የቡርኪናፋሶ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ተራሬ በመከላከያ ትብብር ላይ ከሩሲያ ልዑክ ጋር መምከራቸውን ጽ/ቤታቸው አስታውቋል።
በሞስኮ ምክትል የመከላከያ ሚንስትር የተመራው ልዑክ በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት ቀጣይ ክፍል መሆኑ ታውቋል።
ንግግሩ የመከላከያ እርዳታ ላይ ያተኮረ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ አብራሪዎችን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች የቡርኪናፋሶን ወታደሮች በሩሲያ ለማሰልጠን ውይይት መደረጉ በመግለጫው ተጠቅሷል።
መግለጫው ከዚህ በተጨማሪም የምጣኔ-ሀብት ትብብርና ኒውክሌር ላይ ንግግር እንደነበር ጠቅሷል።
የሩሲያ ልዑክ ጉብኝት ሞስኮ በአፍሪካ ፖለቲካና ምጣኔ-ሀብት ተጽዕኖ ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት አካል ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸው ያለፈው የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን መሪ ፕሪጎዚኒ በቡርኪናፋሶ እንቅስቃሴያቸውን የማስፋፋት ውጥን ነበራቸው ተብሏል።