ፈረንሳይ የቡርኪናፋሶ ኢምባሲዋ እና ሌሎች ተቋማት እንዲጠበቁላት ጠየቀች
ቡርኪናዊያን ፈረንሳይ ከሀገራቸው እንድትወጣ ጫና በመፍጠር ላይ እንደሆኑ ተገልጿል
በቡርኪናፋሶ መዲና የሚገኘው የፈረንሳይ ኢምባሲ በተቃዋሚዎች ጉዳት ደርሶበታል
ፈረንሳይ የቡርኪናፋሶ ኢምባሲዋ እና ሌሎች ተቋማት እንዲጠበቁላት ጠየቀች፡፡
የቶማስ ሳንካራ ሀገር ቡርኪናፋሶ በሀገሯ ያለው የፈረንሳይ ጦር ለቆ እንዲወጣ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ቡርኪናዊያን በኡጋዲጉ በሚገኘው የፈረንሳይ ኢምባሲ ላይ ጥቃቶች በማድረስ ላይ ናቸው፡፡
ፈረንሳይ በቡርኪናፋሶ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች በሚል የሚከሱት ቡርኪናዊያን በሀገራቸው የሚገኙ የፈረንሳይ ትምህርት ቤት፣ የዲፕሎማሲ እና ሌሎች ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በተለይም ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ ቡርኪናዊያን ከሶስት ጊዜ በላይ ጥቃቶችን በፈረንሳይ ተቋማት ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን በሀገራቸው ያለው የፈረንሳይ ጦር ሽብርተኞችን እየረዳ ነው፣ አምባገነኖችን ትረዳለች፣ ሀብታችንን እየመዘበረች ነው እና ሌሎችንም ክሶችን በፓሪስ ላይ አሰምተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ፈረንሳይ ከቡርኪናፋሶ ለቃ እንድትወጣ የጠየቁ ሲሆን በቅርቡ በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት ኢብራሂም ትራውሬ ከሩሲያ ጋር ወዳጅነት መመስረት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
በኡጋዲጉ የሚገኘው የፈረንሳይ ኢምባሲ ለቡርኪና ፋሶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ የሀገሪቱ ወታደራዊ መንግስት ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጠይቋል ተብሏል፡፡
ቡርኪናፋሶ በዓለም አቀፍ ህግ ስምምነት መሰረት የዲፕሎማቲክ ተቋማት ከማንኛውም ጥቃት የመጠበቅ መብት ህግን እንድታከብር ኢምባሲው በጻፈው ደብዳቤ መጠየቁ ተገልጿል፡፡
በፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሚመራው የፈረንሳይ መንግስት በበኩሉ በምዕራብ አፍሪካ የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ጦር በቀጣዮቹ ዓመታት ሙሉ ለሙሉ እንደሚያስወጣ አስታውቋል፡፡
ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ተቃውሞ እየገጠማት ሲሆን የማሊ ወታደራዊ መንግስት ከወራት በፊት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ጦሯን ሙሉ ለሙሉ ማስወጣቷ ይታወሳል፡፡
ከፈረንሳይ ጋር የሰላም አስከባሪ ጦሯን ወደ አፍሪካ ከላኩ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ጀርመን በምዕራብ አፍሪካ ያሰማራችውን ጦር እንደምታስወጣ ከሰሞኑ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል፡፡