የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን መልሶ ግንባታ ሀብት በማሰባሰብ ላይ ናቸው
ሩሲያ በዩክሬን መልሶ ግንባታ እንድትሳተፍ የአውሮፓ ህብረት ጠየቀ፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስምንት ወር የሆነው ሲሆን በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆን አሁን የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ለዩክሬን መልሶ ግንባታ ሀብት በማሰባሰብ ላይ ናቸው፡፡
የህብረቱ የፍትህ ኮሚሽነር ዲደር ሪይንደርስ እንዳሉት ሩሲያ በዩክሬን መልሶ ግንባታ ላይ በፈቃደኝነት እንድትሳተፍ ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለውም የአውሮፓ ህብረት ንብረትነታቸው የሩሲያ መንግስት እና ዜጎች የሀነ ግምታቸው 300 ቢሊዮን ዶላር ሀብት የያዘ ሲሆን ሩሲያ በፈቃደኝት በዩክሬን መልሶ ግንባታ ካልተሳተፈች ይህ ገንዘቧ ለዩክሬን ሊሰጥ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘልንስኪ ከዚህ በፊት በአውሮፓ እና ሌሎች ሀገራት ያሉ የሩሲያ ሀብቶች እንዲታገዱ እና ተላልፈው እንዲሰጧቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከእስካሁኑ በተጨማሪ ንብረትነታቸው የሩሲያዊያን የሆኑ 17 ቢሊዮን ዶላር ሀብት እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን አስታውቋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮንደር ሊን በበኩላቸው ለዩክሬን መልሶ ግንባታ የሩሲያን ሀብት መያዝ ቢያስፈልግም ለዚህ ግን ህግ ሊዘጋጅለት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ የሩሲያዊያንን ሀብት መውረስ እንደማይቻል አስታውቃ ድርጊቱ ከዚህ በፊት የተደረጉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሚጥስ እና በሀገራት እና ተቋማት መካከል አለመተማመኖችን የሚያጠፋ ነው ስትል አስጠንቅቃለች፡፡