ሩሲያዊው ቢሊየነር ሮማን አብራሞቪች የቼልሲ እግር ኳስ ክለብን ለመሸጥ መወሰናቸው አስታወቁ
አብራሞቪች ከሽያጭ የሚገኘውን የተጣራ ገንዘብ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሰለባ የሆኑትን ሰዎች ለማገዝ የሚውል ይሆናል ብለዋል
አብራሞቪች የውሳኔያቸው ምክንያት ግልጽ ባያደረጉም ከሩሲያዊነታቸው ጋር በተያያዘ ማዕቀብን ሽሽት ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው
ሩሲያዊው ቢሊየነር ሮማን አብራሞቪች የቼልሲ እግር ኳስ ክለብን ለመሸጥ መወሰናቸው አስታወቁ፡፡
ሮማን አብርሞቪች በትናትናው እለት እንደገለጹት ከሆነ አንጋፋው የእንግሊዙ ቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ለሽያጭ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
ከቼልሲ የእግር ኳስ ክለብ ሽያጭ የሚገኘውን የተጣራ ገንዘብ “የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ሰለባ የሆኑትን ሁሉ የሚጠቅም ፋውንዴሽን እንዲቋቋምበት መመሪያ ሰጥቻለሁ”ም ብለዋል ሩሲያዊው ቢልየነር አብራሞቪች፡፡
ፋውንዴሽኑ ለጦርነቱ ተጎጂዎች አስቸኳይ እና አፋጣኝ የገንዘብ እርዳታ መስጠትን እንዲሁም የረጅም ጊዜ የማገገሚያ ስራን መደገፍን ያጠቃልላል ሲሉም ተናግሯል፡፡
"ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ሁል ጊዜ ስወስን የክለቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው"ም ነው ያሉት ሩሲያዊው ቢሊየነር አብራሞቪች በሰጡት ጋጤጣዊ መግለጫ፡፡
ውሳኔው ከባድ ቢሆንም የወሰንኩት ውሳኔ አሁን ባለው ሁኔታ ለክለቡ፣ ለደጋፊዎች፣ ለሰራተኞቹ እንዲሁም ለክለቡ ስፖንሰሮች እና አጋሮች የሚጠቅም ነው ሲሉም አክሏል፡፡
አብራሞቪች የውሳኔያቸው ምክንያት ግልጽ ባያደረጉም ከሩሲያዊነታቸው ጋር በተያያዘ ክለቡ የማዕቀብ ሰለባ እንዳይሆን የተደረገ ሊሆን እንደሚችል የሲ.ቢ.ኤስ ስፖርት መረጃ ያመለክታል፡፡
ከአብራሞቪች ውሳኔ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ የእንግሊዝ የህግ ባለሙያ የሆኑት ክሪስ ብራያንት ሩሲያዊው ቢሊየነር ማዕቀብን ፍራቻ ይመስል ሁሉንም ነገር በመሸጥ ላይ ናቸው ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የብሪታኒያው የሌበር መሪ ኬይር ስታርመር አብራሞቪች “ከሩሲያ መንግስት ጋር ባለው ግንኙነት እና ከሙስና ጋር በተያያዘ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን በትናትናው እለት ጠይቀው ነበር፡፡
ጆንሰን ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “በግለሰብ ጉዳዮች ላይ አስተያየት አልሰጥም” ሲሉ ተደምጧል፡፡
ሩሲያዊው ቢሊየነር ከቀናት በፊት ከእንግሊዙ ኃያል ክለብ ቼልሲ የበላይ ጠባቂነት ራሳቸውን ማግለላቸውንና ቼልሲ በክለቡ ቦርድ በጎ አድራጎት ማህበር ሞግዚትነት እንዲተዳደር መወሰናቸው አይዘነጋም፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻን ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም ሀገራትና አጋሮቻቸው በሀገሪቱ ላይ የሚያዘንቡት ዘርፈ ብዙ ማዕቀብ እንደቀጠለ ነው፡፡
በስፖርቱ ዘርፍ ብቻ በርካታ ማዕቀቦች ጥሏል፡፡
በፒተርስበርግ ይካሄድ የነበረው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ወደ ፈረንሳይ ፓሪስ መዛወር፣ የፑቲን ከዓለም አቀፉ የጁዶ ፌዴሬሽን የክብር ፕሬዝዳንትነታቸው መነሳት እንዲሁም ሩሲያ ካለ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር እንዲትጫወት ማድረግ የዓለም አቀፉ የስፖርት አስተዳዳሪ አካል በሩሲያ ላይ ከጣላቸው ማዕቀቦች እንደ አብነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
እንደ ፎርብስ መረጃ ከሆነ የ55 ዓመቱ አብራሞቪች 12.4 ቢልንየን ዶላር የተጣራ ሃብት ያላቸው ናቸው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በባለፈው የ2021 የፈረንጆች ዓመት የቼልሲ ክለብ የሽያጭ ዋጋ 3.2 ቢልዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡