የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የምእራባውያን ዋና አላማ "ሩሲያን መበታተን ነው” አሉ
ፑቲን፤ የኔቶ አባል ሀገራት ዩክሬንን በማስታጠቅ በጦርነቱ እየተሳተፉ መሆናቸው ተናግረዋል
ሩሲያ፤ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ “በአሜሪካ የሚዘወር ዓለም ሊኖር እንደማይችል” በተደጋጋሚ ትገልጻለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የምእራባውያን ዋና አላማ የሩሲያ ፌዴሬሽን መበታተን መሆኑን ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የአሜሪካ እና አጋሮቿ ጥምረት የሆነውን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን /ኔቶ/ አባል ሀገራት ለዩክሬን የጦር መሳሪያን በማቅረብ በጦርነቱ መሳተፋቸውን በገለጹበት ንግግራቸው ነው፡፡
"በአስር ቢሊዮን ዶላር የሚገመቱ የጦር መሳሪያዎች ወደ ዩክሬን እየላኩ ነው። ይህ በእርግጥ ተሳትፎ ነው"ም ነው ያሉት ፑቲን እሁድ እለት ከሩሲያ-1 ቻናል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
የምዕራባውያን ሀገራት አንድ አላማ አላቸው አሱም " የቀድሞዋን የሶቪየት ህብረት እና ዋናውን ክፍል - የሩሲያ ፌዴሬሽን መበታተን ነው" ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ምዕራባውያን ምን አልባትም እኛን ሊቀበሉን የሚችሉት ተበታትነን “በስመ የሰለጠኑ ህዝቦች” ሊሆን ይችላል ያሉት ፑቲን፤ ይህ እውን ሊሆን አይችልም ማለታቸውም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ አሁንም ቢሆን የምትቃወመው ነገር ቢኖር ፤ የአንድ ሀገር የአሜሪካን ጥቅም ብቻ የሚረጋገጥበት ዓለም መኖር አለበት የሚለውን አካሄድ መሆኑም ገልጸዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
" ከሶቪየት ህብረት ውድቀት በኋላ ምዕራባውያን ዓለምን በራሳቸው አምሳያ ለማዋቀር ያደረጉት ሙከራ ወደዚህ ሁኔታ ስላመራን ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለብን" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአሜሪካ የሚዘወር ዓለም ሊኖር እንደማይችል ለፑቲን ቅርብ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞ የሩሲያ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የወቅቱ የሩሲያ ብሄራዊ ደህንነት ምክትል ኃላፊ ዲሜትሪ ሜድቬዴቭ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ከምስራቁ ካምፕ መፈረካከስ በኋላ አሜሪካ ራሷን የዓለም ኃያል አድርጋ እንደምታስብ የተናገሩት ሜድቬዴቭ በዚህ ዘመን ህልሟን እውን ማድረግ አትችልም ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል፡አሜሪካ እና አጋሮቿ “በዩጎዝላቭያ እንዳደረጉት አንደፈለጉ የሚፈነጩበት ዓለም አሁን የለም” የሚል ማስጠንቀቅያ አዘል አስተያየት በመሰንዘር፡፡
እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ሩሲያ የመሳሰሉ ኃያላን ሀገራት ባሉበት፤ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ስህበቱ አሜሪካኖች ከሚያስቡት በተለየ መልኩ የመሆን አድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ጭምር አስረድተዋል ሜድቬዴቭ።