ከጦርነቱ ከአንድ ዓመት በኋላ ቻይና የዩክሬንን ቀውስ ለመፍታት ያላትን ተነሳሽነት በዝርዝር አሳወቀች
ቤጂንግ የዩክሬን ቀውስ ለመፍታት ብቸኛው አዋጭ መንገድ ውይይት እና ድርድር ነው ብላለች
ዩክሬን የቤጂንግን ሰፊ ድጋፍ እጠብቃለሁ ብላለች
ቻይና የዩክሬንን ቀውስ ለመፍታት ተነሳሽነቷን አስታውቃለች።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነቱ ከተጀመረበት አንደኛ ዓመት ጋር በተያያዘ ቤጂንግ ጉዳዩን በሚመለከት መላ ያለችውን ሀሳቧን በዝርዝር አሳትማለች።
በጎርጎሮሳዊያኑ የካቲት 24፤ 2022 የተጀመረውና አሁንም የቀጠለው ጦርነት፤ ቀውሱን ለመፍታት ቻይና ሁለቱን ወገኖች ለማሳመን ያላትን ቁርጠኛነት አሳውቃለች።
ጦርነቱን ለማስቆም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ለዩክሬን ቀውስ "ፖለቲካዊ መፍትሄ" ለመስጠት የቤይጂንግን አቋም የያዘ ጽሁፍ አሳትሟል።
በተለይም የሁሉም ሀገራት ሉዓላዊነት መከበር አለበት የተባለ ሲሆን፤ ወታደራዊ ቡድኖችን በማጠናከር ወይም በማስፋፋት የክልል ደህንነትን ማረጋገጥ አይቻልም ብሏል።
ቤጂንግ "ጦርነቱ መቆም አለበት። የዩክሬን ቀውስ ከቁጥጥር ውጭ መሆን የለበትም" በሚል አቋሟን ገልጻለች።
ቀስ በቀስ ውጥረትን በማርገብ፤ የመጨረሻ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ አለበት፤ የዩክሬን ቀውስ ለመፍታት ብቸኛው አዋጭ መንገድ ውይይት እና ድርድር ነው ብላለች።
በየትኛውም ሀገር የባዮሎጂካል እና የኬሚካል ጦር መሳሪያ ልማትና አጠቃቀምን እንቃወማለን ስትልም አቋሟን ገልጻለች።
በጸጥታው ምክር ቤት ያልተፈቀደውን ማንኛውንም የአንድ ወገን ማዕቀብም እንዲሁ።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቼን ጋንግ ዝርዝር ተነሳሽነቱን ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ ሀገራቸው የዓለም አቀፍ የጸጥታ ተነሳሽነትንም ይፋ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።
ዓለም አቀፋዊ የጸጥታ ተነሳሽነት "የጋራ ትብብር፣ ዘላቂ ደህንነት እና በዓለም ላይ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ በጋራ መስራት" የመሰሉ በርካታ መርሆዎችን የያዘ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም "የክልሎችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ማክበርን፣ በሌሎች ክልሎች ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት እና የዓለም ህዝቦች በራሳቸው ፍቃድ የመረጧቸውን የልማት ዘዴዎች እና ማህበራዊ ስርዓቶችን ማክበር" የሚሉ ጽንሰ-ሀሳቦች ተሰምሮባቸዋል።
የአውሮፓ ህብረት በቻይና የታተመውን የቀውስ መፍቻ "የሰላም ምክረ-ሀሳብ አይደለም" ሲል እርምጃውን ተችቷል።
ዩክሬን በበኩሏ ጦርነቱን ለማቆም ቻይና ዓለም ጥረቶች ላይ ለመሳተፍ ያሳየችውን ተነሳሽነት አድንቃ፤ የቤጂንግን ሰፊ ድጋፍ እጠብቃለሁ ብላለች።