“ኒውክሌርን መታጠቅ እንዲቀር ከተፈለገ አሜሪካ እና ሩሲያ መቅደም አለባቸው”- ቻይና
ቻይና ይህን ያለችው ኃያል ነን ባይ ሃገራት የኒውክሌር ክምችታቸውን ለመቀነስ ቃል በገቡ ማግስት ነው
የኒውክሌር ክምችቷን እያሳደገች ነው መባሉን ያስተባበለችው ቻይና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ማዘመኔን እቀጥላለሁ ብላለች
ቻይና አውዳሚውን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መታጠቅ እንዲቀር ከተፈለገ አሜሪካ እና ሩሲያ ቀድመው እርምጃ ሊወስዱ ይገባል አለች፡፡
ጦር መሳሪያውን ቀድመው በገፍ ያከማቹት እነሱ ናቸው ያለችው ቤጂንግ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን “ማዘመኔን እቀጥላለሁ” ብላለች፡፡
ቤጂንግ ይህን ያለችው ራሷን ጨምሮ አውዳሚውን ጦር መሳሪያ የታጠቁ ኃያል ነን ባይ የዓለም ሃገራት የኒውክሌር ጦርነትንና እሽቅድምድምን ለማስቀረት መስማማታቸውን ባስታወቁ ማግስት ነው፡፡
ቻይናን ጨምሮ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ ትናንት የኒውክሌር አረሮችን ለመቀነስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸው ነበር፡፡ ይህም ምናልባትም ስምምነት ላይ ለመድረስ ወደሚያስችል ስብሰባ ሊያመራ እንደሚችልም ተነግሮ ነበር ምንም እንኳን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የታሰበው ሳይሳካ ቢቀርም፡፡
ቻይና ወታደራዊ ይዞታዎቿን እያጠናከረችና በዘመናዊ መልኩ እየገነባች በሚል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ብዙ ጊዜ መነጋገሪያ አድርጓታል፡፡
በተለይ አምና ከድምጽ በ7 እጥፍ የሚፈጥን ሃይፐር ሶኒክ ሚሳዔል አመረትኩ ስትል ማስታወቋ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡
ከወር በፊት ባወጣችው መግለጫ ቻይና የኒውክሌር ይዞታዋን እያጠናከረች ነው ያለችው አሜሪካ ቤጂንግ በፈረንጆቹ 2027 ሰባት መቶ በ2030 ደግሞ አንድ ሺ የኒውክሌር አረሮችን ልትታጠቅ እንደምትችል ግምቷን አስቀምጣ ነበር፡፡
አሜሪካ በራሷ 3 ሺ 750 ገደማ የኒውክሌር አረሮችን ስለመታጠቋ ይነገራል፡፡ ከዓለም የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ክምችት 90 በመቶ ያህሉ በአሜሪካ እና ቻይና የተያዘ ነው የሚሉም አሉ፡፡
የኒውክሌር ይዞታዋን እያጠናከረች ነው መባሉን ያስተባበለችው ቻይና በበኩሏ በትንሹ ደህንነቷን ለማስጠበቅ የሚያስችላትን ኒውክሌር ለመታጠቅ እየሰራች መሆኗን አስታውቃለች፡፡
የኒውክሌር ይዞታዋ እንዲያው ከሳታላይት በሚገኙ መረጃዎች ብቻ ብዙ ነው እየተባለ የሚነገርለት እንዳልሆነም አስታውቃለች፡፡
ቤጂንግ ኃያል ነን ባይ ሃገራቱ የኒውክሌር ክምችታችንን እንቀንስ ማለታቸውን አትቀበልም፡፡ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿን የበለጠ እንደምታዘምንም ነው ያስታወቀችው፡፡
የኒውክሌር ይዞታዬ እንዲቀንስ ከተፈለገ በቅድሚያ አሜሪካ እና ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ክምችታቸውን ይቀንሱ ስትልም ጠይቃለች፡፡
ኒውክሌርን የታጠቁት አምስቱ ኃያላን ሃገራትም አሜሪካ በጃፓን ተጠቅማው ከፍተኛ ውድመት ያደረሰችበትን ይህን አውዳሚ ጦር መሳሪያ ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ከአሁን ቀደም ደጋግመው ቃል ገብተዋል፤ ምንም እንኳን ቃል በተግባር ባይገለጥም፡፡