የዩክሬን ጦርነት ለአሜሪካ ጦር መሳሪያ ሽያጭ ትልቅ የገበያ እድል መፍጠሩ ተገለጸ
አሜሪካ ከዓለም ጦር መሳሪያ ሽያጭ ውስጥ 40 በመቶውን ተቆጣጥራለች ተብሏል
በዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ምክንያት የተራቆቱት አውሮፓውያን የአሜሪካንን ጦር መሳሪያ በገፍ በመሸመት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል
የዩክሬን ጦርነት ለአሜሪካ ጦር መሳሪያ ሽያጭ ትልቅ የገበያ እድል መፍጠሩ ተገለጸ።
በአውሮፓ ምድር ለአንድ ሳምንት ተብሎ የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አንድ ዓመት አልፎትም መቋጫ አላገኘም።
- የሩሲያው ፓትሪያርክ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ባላት ቤተክርስቲያን ላይ የምትፈጥረውን ተጽእኖ እንድታቆም ጠየቁ
- የዩክሬንን ወታደሮች ከባክሙት ከተማ አያፈገፍጉም ሲሉ ዜለንስኪ ተናገሩ
ይህ ጦርነት የዓለም ንግድን እና ዲፕሎማሲን ያናጋ ሲሆን በተለይም የምግብ እና ነዳጅ ዋጋን አንሮታል።
ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን መላኳ ጦርነቱ በሩሲያ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ የዩክሬን እጣ ይደርሰናል ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።
ይህንንም ተከትሎ ያላቸውን የጦር መሳሪያ ለዩክሬን የለገሱ የአውሮፓ ሀገራት አሁን ላይ አነስተኛ የጦር መሳሪያ ክምችት እንዳላቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህንንም ተከትሎ እነዚህ የአውሮፓ ሀገራት ከአሜሪካ የጦር መሳሪያ ግዢ በመፈጸም ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ምክንያት አሜሪካ ከዓለም ጦር መሳሪያ ንግድ ውስጥ 40 በመቶ ድርሻውን ተቆጣጥራለች ተብሏል።
የስቶኮልም ዓለም አቀፍ ሰላም ኢንስቲትዩት ባወጣው ሪፖርት መሰረት የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ለአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ትልቅ ሲሳይ ይዞ መምጣቱን አስታውቋል።
የአውሮፓ ሀገራት የጦር መሳሪያ ግዢ ፍላጎታቸው ካለፉት አምስት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ65 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ተቋሙ በሪፖርቱ ገልጿል።
የዓለም ሀገራት የጦር መሳሪያ ፍላጎት እያደገ መምጣት እንዳሳሰበው የገለጸው ይህ የሰላም ተቋም ፍላጎቱ ከዚህ በፊት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ እንደነበር ጠቁሟል።