ጀርመን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 900 ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣ ተገለጸ
ጀርመን በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ውስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት ካልሰጠች ጉዳቱ አየጨመረ እንደሚሄድ ጥናት አሳስቧል
አውሮፓ ባሳለፍነው ዓመት በታሪክ ከፍተኛ ሙቀት ማስመዝገቧ ይታወሳል
ጀርመን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 900 ቢሊዮን ዶላር እንደምታጣ ተገለጸ።
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቷ ጀርመን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ኢኮኖሚዋ ክፉኛ ሊጎዳ እንደሚችል የሀገሪቱ አካባቢ ጥበቃ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴሮች አስታውቀዋል።
ተቋማቱ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቆጣጠር በጋራ ያስጠኑትን ጥናት ይፋ ያደረጉ ሲሆን ሀገሪቱ ለታዳሽ ሀይል ትኩረት እንድትሰጥ አሳስበዋል።
- በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 113 ሚሊዮን አፍሪካውያን ሊሰደዱ ይችላሉ ተባለ
- የአውሮፓ ሕብረት፤ በአውሮፓ በ 500 ዓመት ውስጥ “አስከፊ” የተባለ ድርቅ መከሰቱን ገለጸ
በዚህ ጥናት መሰረትም ጀርመን በቀጣዮቹ 25 ዓመታት ውስጥ አሁን ባለችበት ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ 900 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች።
በመሆኑም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሀይል አጠቃቀምን ማዘመን፣ የበካይ ጋዝ ቁጥጥር እና ሌሎች ስራዎችን ልታከናውን እንደሚገባም ጥናቱ አሳስቧል ሲል ዶቸ ቪለ ዘግቧል።
ነገር ግን ጀርመን ጥብቅ የአየር ንብረት ለውጥ መቆጣጠሪያ ፖሊሲዎችን ካልተገበረች ከፍተኛ ሙቀት፣ በጎርፍ መጥለቅለቅ እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳቶችን ልታስተናግድ እንደምትችል ተገልጿል።
እንዲሁም የጀርመን ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት በዚሁ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እስከ 2 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ ይችላልም ተብሏል።
በመሆኑም በከተሞች አረንጓዴያማ ስፍራዎች ማስፋት ከተቻለ እና ሌሎች የታዳሽ ሀይል ፕሮጀክቶች ከተተገበሩ ጉዳቱን እስከ 60 በመቶ እና ከዛ በላይ መቀነስ እንደሚቻል ተገልጿል።
የአየር ንብረት ለውጡ ከኢኮኖሚ በተጨማሪም የሟቾችን ቁጥር በመጨመር እና የዜጎችን ህይወት የማወሳሰብ አቅም እንዳለውም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
አውሮፓ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ባስመዘገበው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት አህጉሪቱ ለሰደድ እሳት አደጋ እና ውሃ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን ፖርቹጋል፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ብሪታንያ የአደጋው ዋነኛ ሰለባዎች ነበሩ።