75 በመቶ ዴሞክራቲክ መራጮች በሚቀጥለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አዲስ ሰው እንደሚፈልጉ ተገለፀ
በተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት መራጮቹ ከጆ ባይደን ይልቅ ሌላ ሰው ፕሬዝዳት እንዲሆን ይፈልጋሉ
ዴሞክራቲክ የሆኑና የዴሞክራቲክ ዝንባሌ ያላቸው መራጮች 3/4 በ2024 አዲስ ፊት ይፈልጋሉ
75 በመቶ ዴሞክራቲክ መራጮች በሚቀጥለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ውጪ ሌላ ሰው ፕሬዝዳንት እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው ተገለፀ።
ሲ.ኤን.ኤን አዲስ ያሰባሰበው የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው ሶስት አራተኛ የሚሆኑት ዲሞክራቲክ የሆኑና ዲሞክራቲክ ዝንባሌ ካላቸው መራጮች በ2024 አዲስ ፊት ይእንደሚፈልጉ ያመላክታል።
የሕዝብ አስተያየት ውጤቶቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተቀባይነት ዝቅተኛ መሆኑን እና በመቶኛ ሲለካም በ30ዎቹ ውስጥ እንደሚገኝ ነው ተብሏል።
ይህ ሊሆን የቻለውም አብዛኞቹ አሜሪካውያን በሀገሪቱ እና በኢኮኖሚው ሁኔታ ቅር በመሰኘታቸው እንደሆነም ነው ሲ.ኤን.ኤን የዘገበው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተወዳጅነት እና ተቀባይነት በ2020 ድጋፍ በሰጧቸው ደጋዎቻቸው ዘንድ ጭምር እያሽቆለቆለ መምጣቱም ተነግሯል።
ከዚህ ቀደም ከአሜሪካው ዴሞክራት ፓርቲ አባላት በተሰበሰበው ድምጽ አብዛኞቹ ዴሞክራቶች በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ባይደን በሌላ ሰው እንዲተኩ ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለፀ።
የኒው ዮርክ ታይምስ ሲዬና ኮሌጅ ከዴሞክራቶች ባሰባሰበው እና ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ 64 በመቶ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ለ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከባይደን ይልቅ ሌላ እጩ መቅረብ እንዳለበት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አጠቃላይ ተቀባይነት ደረጃ በ33 በመቶ መሆኑም በተሰበሰበው ህዝብ አስተያየት ተመላክቷል።
የኑሮ ውድነት፣ የኣለም አቀፍ ቀውስ፣ በቅርቡ የአሜሪካ ፍርድ ቤት ለሴቶች የተሰጠውን ህገ መንግስታዊ የውርጃ መብት መግፈፍ ለፕሬዝዳንት ባይደን ተቀባይነት መቀነስ በምክንያትነት ተቀምጠዋል።