ኮሚሽኑ በመጀመሪያ ዙር 75ሺ የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎችን 'ዲሞቢላይዝ' የማድረግ ስራ ነገ እጀምራለሁ አለ
በመጀመሪያው ዙር ወደ ስልጠና ካምፕ የሚገቡ ታጣቂዎች በነገው እለት ትጥቃቸውን ለመከላከያ ስራዊት ያስረክባሉ ብሏል
ኮሚሽኑ ከ7 ክልሎች የተውጣጡ ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ለመበተን እና መልሶ ለማቋቋም እየሰራሁ ነው ብሏል
የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በመጀመሪያው ምዕራፍ 274 ሺህ ታጣቂዎች በሚገኙበት ትግራይ ክልል 75ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ወይም ወደ ማህበረሰብ የመቀላቀል ስራውን በነገው እለት በይፋ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ፕሮግራምና ፕሮጀክቶች በመቅረጽ ከሰባት ክልሎች ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከ760 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በሁለት ዓመታት ውስጥ የዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ስራውን ለመጨረስ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል።
ህዳር12/ 2017 ዓ/ም ጀምሮም ለመጀመሪያው ዙር ዲሞቢላይዜሽን ማስፈጸሚያ ሀብት መንግስትና ከለጋሾች ማግኘት ተችሏል ብሏል።
መንግስት ኮሚሽኑ ስራ ሲጀምር 1 ቢሊዮን ብር የተለገሰ ሲሆን በተጨማሪም ከ7 ሀገራት 60 ሚሊየን ዶላር ተገኝቷል።
በድጋፍ የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት የገንዘብ እና የቁስ ድጋፍ ማድረጋቸው ሲገለጽ ወደ 12 የሚጠጉ ሀገራት ደግሞ በቀጣይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ተብሏል።
ኮሚሽኑ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ስራው ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር እና ከሚመለከታቸው የፌዴራል ተቋማት ጋር በመሆን የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎችን መለየት መቻሉን እና ሶስት የዲሞቢላይዜሽን ማዕከላትንም መረከቡን ገልጿል።
ኮሚሽኑ እንደገለጸው በትግራይ ክልል መቀሌ ፣ እዳጋ ሀሙስ እና አድዋ የመጀመሪያ ዙር ተዋጊዎች ስልጠና የሚወስዱባቸው አካባቢዎች ናቸው።
በመጀመሪያ ዙር ለ75 ሺህ ታጣቂዎች በአራት ወራት ስልጠና ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል።
የተሃድሶ ስልጠና ሰነዶች ዝግጅትና የአሰልጣኞች ስልጠና፤ የመመዝገቢያ ሶፍትዌር ማበልጸግ የማዕከላት ርክክብና ጥገና እንዲሁም አስፈላጊ የሎጅስቲክስ ግጞዥና አቅርቦት መከናወኑ ነው የተነገረው ፡፡
በዚህ መሰረት የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ወደ ማዕከላት ሲገቡ የስድስት ቀናት የተሃድሶ ቆይታ ይኖራቸዋል።
በቆይታቸውም የዲጅታል ምዝገባና ማረጋገጥ፣ የሳይኮ-ሶሻል እና የሲቪክ ተሃድሶ ስልጠና ይወስዳሉ ተብሏል፡፡
የተሃድሶ ፕሮግራም ተሳታፊዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲመለሱ ለመሠረታዊ ፍጆታ እንዳይቸገሩ የመልሶ ማቀላቀል ክፍያ ተሰጥቷቸው ወደ ማህበረሰቡ ይሸኛሉ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ለሁለት አመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በህዳር 2015 በፕሪቶሪያ በተካሄደው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተቋጭቷል።
በዚህ ሰምምነት መሰረት ህወሓት ትጥቅ ለመፍታታ የተስማማ ሲሆን የፌደራል መንግስት ይህን እንዲያስፈጽም ኮሚሽኑን ማቋቋሙ ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ስምምነቱን በተገቢው ሁኔታ ባለመፈጸም እርስበእርስ ሲወቃቀሱ ይደመጣሉ።