ህውሓት ክልሉን ወደ ብጥብጥ ሊወስዱ ከሚችሉ ውሳኔዎች እንዲቆጠብ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አሳሰቡ
ህውሓት አወዛጋቢውን የፓርቲው 14ኛ ጉባኤ ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል
ህውሓት እያደረገ ያለው ጉባኤ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አባላት የፓርቲ ተቀባይነት ማሳጣት እና አስተዳደሩን ለመቆጣጠር ከመፈለግ የመነጨ እንደሆነ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ላለፉት አምስት አስርተ አመታት ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ የዘለቀው ህውሓት ከፌደራል መንግስት አስተዳደር ከወረደም በኋላ ማዕከላዊ አጀንዳ መሆኑን ቀጥሏል።
ከሰሞኑ በፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት መመለስ እና ድርጅታዊ ጉባኤን በማካሄድ መካከል በድርጅቱ ዋና ሰዎች መከፋፈል መፈጠሩን ተከትሎ በክልሉ ውጥረት እንዲባባስ አድርጓል።
በድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን ፓርቲው ከምርጫ ቦርድ እንዲመለስለት የጠየቀው ህጋዊ ሰውነት ሙሉ ለሙሉ ምላሽ ባያገኝም ድርጅታዊ ጉባኤውን ከማካሄድ ወደ ኋላ አላለም።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ድግሞ ጉባኤው እየተካሄደ ያለበት ሂደት፣ በፓርቲው ህጋዊ ስውነት ማስመለስ ዙርያ በቀረቡ ሰነዶች እና ሂደቶች ላይ ቅሬታ አለን በማለት ከጉባኤው እራሳቸውን አግልለዋል።
አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 14 የሚሆኑ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ፓርቲው ከሚያካሂደው ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን ይፋ ያደረጉት ባለፈው እሁድ እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ ነበር።
ባሳለፍነው ማክሰኞ ድርጅቱ ጉባኤውን ማካሄድ መጀመሩን ተከትሎ ህውሓት በማካሄድ ላይ የሚገኝው ጉባኤ ትግራይን እና ህዝቡን ወደ አደጋ ከመክተት የዘለለ እርባና እንደሌለው ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎ በክልሉ እያየለ የሚገኝው ውጥረት ወዴት የሚወስድ ነው? ክልሉ ወደ ዳግም ግጭት እንዳይገባስ ምን መደረግ አለበት? ሲል አል ዐይን አማረኛ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን አነጋግሯል።
የሳልሳይ ወያኔ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ብርሀኔ አጽብሀ እየተመለከትን ያለው ነገር ህውሓት ከስህተት የማይማር እና ለህዝቡ ምንም ግድ እንደሌለው የሚያመላክት ነው ብለዋል።
“ችግሩ የሚጀምረው ከፕሪቶርያው ስምምነት በኋላ ማድረግ ከጀመረው የፓርቲ ግምገማ ነው፤ ባለፉት ሶስት አመታት በጦርነት ውስጥ የማቀቀ፣ የመልሶ ማቋቋም የህግ እና ስርአት መከበር፣ የፕሪቶርያውን ስምምነት በተገቢው ልክ ማስፈጸም፣ በጎረቤት ሀገራት የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ እና ሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎችን መመለስ ሲገባው ድርጅቱ በቀጣይነቱ ላይ ለምምክር ከሶስት ወር በላይ አዳራሽ ዘግቶ ስብሰባ መጀመሩ ከስልጣኑ ያለፈ ለህዝብ እንደማይቆረቆር ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፓርቲው ባደረገው የግምገማ መድረክ ላይ ልዩነቶችን ከማጥበብ ይልቅ ከዛ በከፋ እንዲለያይ እና ቡድን እንዲመሰረት ያደረገው እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ብርሀኔ፤ ከጉባኤው በኋላ በጊዜያው አስተዳደሩ እና በእነ ዶክተር ደብረጽዮን መካከል ይታይ የነበረውን ልዩነት ለአብነት አንስተዋል።
አክለውም “ከጦርነቱ መቆም በኋላ የስልጣናቸው ቀጣይነት ላይ ለመምከር ለ3 ወራት የተሰበሰቡትን ያህል የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ህዝብን በተመለከተ ለአንድ ሳምንት እንኳን ተሰብስበው የሚያውቁ አይመስለኝም” ብለዋል።
“ህወሓት አይደለም ለሁለት ለአራት ቢከፈል የእኛ ጉዳይ አይደለም፤ እኛን የሚያሰጋን አቅም ባጠረው እና መከፋፈል በገጠመው ጊዜ ሁሉ ወደ ህዝቡ የሚያወርዳቸው ውዝግቦች የሚፈጥሯቸው ችግሮች ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
የሳልሳይ ወያኔ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ብርሀኔ እንደሚሉት “በመጀመርያም ቢሆን የሶስት አመቱን ጦርነት ካስከተሉ ምክንያቶች መካከል ምርጫ አደርጋለሁ እና አታደርገም በሚል የተፈጠረው ውዝግብ ዋነኛው ነው።
“ካሳለፍነው ችግር ሙሉ በሙሉ ባላገገምንበት ሁኔታ ፓርቲው በራሱ የገባበት መከፋፈል እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ከሚገኝበት ውዝግብ መካከል ጉባኤውን ማካሄዱ የክልሉን ውጥረት አባብሶታል”ባይ ናቸው።
በዚህም መሰል የቃላት ምልለሶችና እና ውጥረቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ የእርሳቸውንን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ስጋት መሆኑን ጠቁመዋል ።
ሌላኛው በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀው ፓርቲ ባይቶና ምክትል ሊቀመንበር ዮሴፍ በርኸ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲመሰረት በህውሓት የበላይነት እንዲቋቋም መደረጉ፣ የሲቪል ማህበረሰብ አካላት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አለመወከላቸው ክልሉ አሁንም በአንድ ፓርቲ እሰጣ ገባ ችግር ውስጥ እንዲገኝ ያደረገው ነው ባይናቸው።
ምክትል ሊቀመንበሩ አክለውም ፓርቲው አሁን ላይ ለሁለት ተከፍሎ የሚወዛገብበት ጉዳይ የህጋዊ ሰውነት እና የጉባኤ አጀንዳ ሳይሆን፤ ስልጣንን ይዞ መቀጠል በሚፈልገው የጊዜያው አስተዳደሩ አባላት እና ከጦርነቱ ማቆም በኋላ ከስልጣን ተገፍተል በሚሉ ወገኖች መካከል የሚደረግ እንደሆነ ይናገራሉ።
“የፕሪቶርያው ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ከስልጣን የተገፈው የደብረጽዮን ቡድን ባለፉት ጊዜያት ጊዜያው አስተዳደሩ ላይ ህዝቡ እምነት እንዳይኖረው እና የመወሰን አቅሙ እንዲገደብ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርግ እኛም የምንታዘበው ነው፤ አሁንም ድርጅታዊ ጉባኤ አደርጋለሁ ብሎ መነሳቱ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አባላት የፓርቲ ተቀባይነት ማሳጣት እና አስተዳደሩን ለመቆጣጠር ከመፈለግ የመነጨ እንደሆነ ይሰማኛል” ነው ያሉት።
የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ ሲቀጥሉ ፓርቲው እየካሄደ የሚገኝው ጉባኤ ህገ ወጥ እንደሆነ በህግ ተደንግጎ ሳለ በማን አለብኝነት ወደ ጉበኤ መግባቱ ልዩነቶችን ከማስፋት እና ከፌደራል መንግስት ተቋማት ጋር ከመቃረን ባለፈ የተለየ መልካም ውጤትን የማያስገኝ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት ፓርቲው እየተወዛገበበት የሚገኝው ጉዳይ አንድም ከህዝብ ጥቅም ጋር የሚያገናኝው ጉዳይ የለም ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ ፤በተለይ ክልሉ በተራዘመ ጦርነት ውስጥ በርካታ ችግርን እንደማሳለፉ አሁን ላይ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለፖለቲካ ሳይሆን ለህዝብ መሆን ነበረበት ብለዋል።
ፓርቲው እየተነታረከበት የሚገኝው ጉዳይ ወደ ህዝብ ወርዶ ጎራ ወደ መለየት እና ህብረተሰቡ የውዝግቡ ሰለባ እንዳይሆን ፓርቲው የገባበትን ችግር በራሱ እንዲወጣ ህዝቡን የማንቃት እና የማስተባበር ስራ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ አቶ ዮሴፍ ነግረውናል።
አክለውም “ነገሩ የአንድ ፓርቲ እንጂ የህዝብ ጉዳይ አይደለም፤ የፌደራል መንግስቱ ፓርቲውን አንድ እራሱን የቻለ ተቋም መሆኑን በመገንዘብ እንደባለፈው አይነት ችግር እንዳይፈጠር ከሚሉ በህዝብ ላይ ካነጣጠሩ ዛቻ እና ፕሮፖጋንዳዎች ሊቆጠብ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል።
ህግ እና ስርአትን ማስከበር ካለበትም ከፓርቲው ጋር በተገቢው መንገድ ይነጋገር እንጂ ከህዝብ ጋር የሚያገናኝው ወደ ድጋሚ ግጭት ውስጥ የምንገባበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፤ የትግራይ ህዝብም በህውሓት ምክንያት ተጨማሪ ዋጋ የሚከፍልበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም” ነው ያሉት።
ህውሓት አወዛጋቢውን የፓርቲው 14ኛ ጉባኤ ካሳለፍነው ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም ጀምሮ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር “ህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት መከልከል ማለት ውሉን ማፍረስ ነው፤ ፓርቲው የሚፈርስ ከሆነ የትግራይን ሕዝብ ለበላተኛ አሳልፎ መስጠት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
እስከዛሬ በነበረው አሰራር የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚመረጡበት ይህ ጉባኤ የፓርቲውን ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጌታቸው ረዳን ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሊያነሳ እንደሚችል ይገመታል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የህውኃትን ጉባኤ አስመለክቶ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ህወሓት የቦርዱን ማሳሰቢያ ወደ ጎን በመተው ጉባኤውን ካደረገ፣ ለጉባኤው እና በጉባኤ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች እውቅና እንደማይሰጥ አሳስቦ ነበር።
ይህን ተከትሎም የመንግስት ኮምንኬሽን ሚንስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ህግና ስርዓትን አክብሮ የማይንቀሳቀስ የትኛውም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ጥፋት ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ለገሰ “ አንዴ፣ ሁለቴ፣ መሳሳት ያለንና የነበረ ነው፤ በተመሳሳይ መንገድ ተመሳሳይ ስህተት ሶስቴ መፈጸም ግን የመጨረሻው የጥፋት መንገድ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ብቻኛው ተጠያቂ እራሱ ይሆናል” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።