ጌታቸው ረዳ በዴላ በኩል በእግር ከሸሹት የህወሓት ቡድን አባላት መካከል ናቸው ተባለ
ተሽከርካሪዎቹ ከማይጨው 60 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ዴላ ወረዳ ነው የተያዙት
ቡድኑ ለመሸሽ የተጠቀመባቸው ናቸው የተባሉ 40 ተሸከርካሪዎች ተይዘዋል
የህወሓት ስራ አስፈጻሚ አባል እና የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አማካሪ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በዴላ በኩል ከሸሹት የህወሓት ቡድን አባላት መካከል ናቸው ተባለ፡፡
አቶ ጌታቸው ከሸሸው ቡድን ጋር እንደነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡
የቀድሞው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ክንደያ ገብረህይወት (ፕ/ር) ፣ የማይጨው አስተዳዳሪ የነበረው አቶ ሀፍቱ ኪሮስ እና ሌሎች የወረዳ አመራር የነበሩ ሰዎች የህወሓት ቃል አቀባይ ከነበሩት አቶ ጌታቸው ጋር ከሸሹት መካከል ናቸው፡፡
ይህም ቡድኑ ሰራዊቱን መቋቋም ተስኖት ወደ ገጠራማ ስፍራ በእግር መጓዝ ሲጀምር ጥሏቸው በሄዳቸው ሰነዶች ለማረጋገጥ ተችሏል የ32ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ ገለጻ፡፡
ቡድኑ በታጣቂዎቹ በኩል ለማጥቃት ቢሞክርም አልተሳካለት ያሉት ኮሎኔል ደጀኔ የቡድኑ መሪዎች በእግራቸው መሸሽ ከመጀመራቸው በፊት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ከ40 በላይ ተሽከርካሪዎች በሰራዊቱ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን በስፍራው ለሚገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የመንግስት እና የግል ናቸው የተባሉት ተሽከርካሪዎቹ የቡድኑ ከፍተኛ አመራች በእግራቸው በሸሹባት በዴላ ወረዳ ነው የተያዙት፡፡
ዴላ ከማይጨው በ60 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
ተሽከርካሪዎቹን ከፅንፈኛው ቡድን ሀይሎች አስጥሎ በቁጥጥር ስር ያዋለው ሰራዊቱ ባደረገው ፍተሻ ቀደም ሲል በእግራቸው ስለመሸሻቸው የተነገረላቸውን ሰዎች መታወቂያ እና ፓስፖርቶች ስለማግኘቱም ነው አዛዡ የተናገሩት።
እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ በሰራዊቱ ከተያዙት ተሽከርካሪዎች መካከል ስድስቱ በአሻራ የሚከፈቱ እጅግ ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ሲሆኑ አራቱ ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ስራ በሚል ከፌደራል መንግስቱ ለትግራይ ክልል የተበረከቱ አምቡላንሶች ናቸው።
ሰራዊቱ ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ የጭነት ተሽከርካሪዎችን እና ቦቴዎችን ወደ ማይጨው ከተማ እንዲገቡ አድርጓልም ብለዋል ኮሎኔሉ።
በአሻራ የሚከፈቱትን ተሽከርካሪዎች ከሞኤንኮ ጋር በመነጋገር ከአካባቢው ለማንሳትና ፍተሻ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።