“ቡድኑ አማጺ ሆኖ በተራዘመ የሽምቅ ውጊያ ውስጥ ሊቆይ የሚችልበት እድል ተሟጧል”- መንግስት
ቡድኑ ተሸንፎ ለውዥንብር መዳረጉንም ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል
“ቡድኑ አማጺ ሆኖ በተራዘመ የሽምቅ ውጊያ ውስጥ ሊቆይ የሚችልበት እድል ተሟጧል”- መንግስት
የህወሓት ቡድን አማጺ ሆኖ በተራዘመ የሽምቅ ውጊያ ውስጥ ሊቆይ የሚችልበት እድል መሟጠጡን የጠቅላይ ሚኒት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ ንጹሃን ሳይጎዱ እና ንብረት ሳይወድም መቀሌን ለመቆጣጠር የተቻለበት የህግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው ወንጀለኛው ቡድን የካበተ የጦር ልምድ እንዳለው እና እንደታጠቀ በማስመሰል ወደተራዘመ የሽምቅ ውጊያ ሊገባ እንደሚችል ውሸት ሲነዛ ነበር ያለ ሲሆን ስልታዊ ማፈግፈግ እንዳደረገ ሲለገልጽ እንደነበርም ገልጿል፡፡
ሆኖም ይህ ከእውነት የራቀ ውሸት ነው ጽህፈት ቤቱ እንዳለው፡፡
ቡድኑ ተሸንፎ ለውዥንብር መዳረጉን እና ከአሁን በኋላ በተራዘመ አመጽ ውስጥ ሊቆይ የሚችልበት ዐቅም እንደሌለውም አስታውቋል፡፡
“ውሸት እና ስርዓት አልበኝነት በያኔው የቡድኑ የሽምቅ የትግል ዘመን ሰርቶ ሊሆን ይችላል”ያለው ጽህፈት ቤቱ ቡድኑ “ከዚህ ሊማር አልቻለም” ብሏል በመግለጫው፡፡
ቡድኑ “ለውጥ ጠል” መሆኑን ተከትሎ ፍትሃዊ ኢትዮጵያን በመፍጠሩ ሂደት አስተማማኝ አጋር ሊሆን አይችልምም ነው ጽህፈት ቤቱ ያለው፡፡
የትግራይ ህዝብ ከየትኛውም ጉዳይ በላይ አካታች እና ፍትሃዊ እድገት፣ ሰላም፣ ነጻነት እና ደህንነትን እንደሚሻም አስቀምጧል፡፡
“ቅቡልነት ያለው እና ትክክለኛ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ፤ በውስጥም በውጪም ጥቂት ደጋፊዎች ያሉት እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የሚገኝ ‘አድሃሪ’ ቡድን በተራዘመ አመጽ ውስጥ ሊዘልቅ ፈጽሞ አይችልም” ሲልም ነው መግለጫው ያተተው፡፡
ቡድኑ ግጭቱን ዓለማቀፋዊ መልክ ለማስያዝ ያደረገው ጥረት ከተጠያቂነት ለማምለጥ ያደረገው የመጨረሻ ሙከራ እንደሆነ እና ለንጹሃን ይቆረቆራል ማለቱ “ጥንተ ተፈጥሮውን አለማወቅ”እንደሆነም ገልጿል፡፡
ለዚህም ከመከላከያው መጠቃት ባለፈ በማይካድራ የተፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ እና ሌሎችንም ምክንያቶች በማሳያነት አስቀምጧል፡፡
ቡድኑ ስለ ንጹሃን ደህንነት ሊቆረቆር የሚችልበት “ምንም ዓይነት የሞራል ልዕልና” እንደሌለውም ነው የገለጸው፡፡
ለዚህም በስልጣን ላይ የቆየባቸው ሶስት ገደማ አስርት ዓመታት ምስክሮች ናቸው ብሏል፡፡
ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው የፌዴራል መንግስቱ አሁንም ቢሆን ለዜጎች ደህንነት መጠበቅ ቅድሚያ ይሰጣል ያለም ሲሆን ከአሁን በኋላ ያለው ስራ ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ፣ ህግ እና ስርዓትን ማስፈን፣ ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረስ፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም እና በቡድኑ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት እንደሆነ አስታውቋል፡፡