ጥቃቱ የተፈጸመው አስቀድሞ ቤቶች “በብሄርና ሃይማኖት” ከተለዩ በኋላ ነው-ተጎጅዎች
ተጎጂዎቹ ግድያና ዘረፋውን ፖሊስና ልዩ ኃይል ማስቆም ይችል ነበር የሚል ቅሬታም አቅረበዋል
በብጥብጡ ወቅት ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ አካለትን ጨምሮ ከ7ሺ በላይ ተጠርጣሪ ግለሰቦች መያዛቸውን የኦሮሚያ ክልል ገልጿል
በብጥብጡ ወቅት ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ አካለትን ጨምሮ ከ7ሺ በላይ ተጠርጣሪ ግለሰቦች መያዛቸውን የኦሮሚያ ክልል ገልጿል
ከአርቲስት ሀጫሉ ሁነዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ክልል በተፈጸሙ ጥቃቶች የሕይወት መጥፋትና የአካል መጉደል እንድሁም የንብረት ውድመት መድረሱ ይታወሳል፡፡
የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በተፈጠረ ብጥብጥ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል 239 ሰዎች መሞታቸውን የመንግስት ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
የጉዳቱ ሰለባዎች የክልሉ የጸጥታ ሀይሎች ጉዳቱን ማስቆም አለያም መቀንስ ይችሉ ነበር የሚል ቅሬታ አሰምተዋል፡፡
በተለይም በምዕራብ አርሲ ዞን፣ በባሌ ዞንና በአርሲ ዞን ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የደረሰባቸው በደል እጅግ የከፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡በአንዳንድ አካባቢዎችም የመንግስት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሲሆን በተለይ በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ 38 ተቋማት የወደሙ ሲሆን 192 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረትም መውደሙን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡
በምዕራብ አርሲ ዞን ከሻሸመኔ 25 ኪሎ ሜት ርቀት ላይ በምትገኘው ኮፈሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና በመንግስት ሥራ ላይ የተሰማሩት ስማቸው ለዚህ ዘገባ እንዳይጠቀስ የጠየቁት ግለሰብ ሁኔታው እጅግ አደገኛ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በኋላ በአካባቢው ብቻ ሳይሆን በዞኑም ጭምር ላለመኖር መወሰናቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ሰኔ 23 ቀን ከ6 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ ጥቃት መፈጸሙን ያነሱት የኮፈሌው ነዋሪ እርሳቸው ተከራይተው በሚኖሩበት ግቢ ላይ ቃጠሎ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ መጀመሪያ እርሳቸው ተከራይተው የሚኖሩበት ግቢ “የአማራ ነው” በሚል አስቀድሞ ጥቆማ እንደተሰጠ ያነሱት ግለሰቡ “እኔ ራሴ ኦሮሞ ብሆንም” ከባድ ችግር ግን ገጥሞኛል ሲሉ የደረሰባቸውን ችግር ይናገራሉ፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንደሳ በድንገተኛ መገደልን ተከትሎ ከገጠርና ከከተማ ተውጣጡ ሰዎች ጥቃት መፈጸማቸውን ያነሱት ነዋሪው እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ የሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣ ረጅም ጊዜ የተለፋት የሀገር ሀብትና ንብረት መውደሙን አንስተው እርሳቸው ሰባት ዓመት በመንግስት ተቀጥረው ያፈሩትን ንብረትና ይኖሩበት የነበረው ቤት ሙሉ ለሙሉ መውደሙን አንስተዋል፡፡
አስተያየት ሰጭው ጥቃት አድራሾቹን ለማስቆም የትኛውም የመንግስት አካል አለመምጣቱን ያኑሱ ሲሆን ለዚህ እርሳቸው ተጠያቂ የሚያደርጉት የዞንና የወረዳ አስተዳደሮችን ስለመሆኑ ተናረዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጭ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪው አቶ ከፍያለው በከተማው በሆቴልና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን በሰሞኑ ችግር ከ52 ሚሊዮን በላይ ንብረታቸው መውደሙን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
የጥቃቱ ምክንያት የሃይማትና የብሔር መሆኑን ያሱት አቶ ከፍያለው በእርሳቸው ድርጅት ተቀጥረው የነበሩ ሰራተኞችም መበተናቸውንና ከስራ ውጭ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
“ረጅም ሰዓት ጥቃት ሲደረግ መንግስት ለምን ዝም አለ” የሚል ቅሬታ
አስተያየታቸውን ለአል አይን የሰጡት ሁለቱም ግለሰቦች በአካባቢዎቹ የደረሰውን ችግር መንግስት መዋቅር ማስቆም ወይም መቀነስ ይቻል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተለይም የኮፈሌው ነዋሪ በቅርቡ ሰልጥነው የጨረሱ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት ጥቃት እየተፈጸመ እያለ እያዩ እንደነበር ገልጸው ይህንን ለማስቆም ግን ምንም ጥረት አለማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ችግሩን ማስቆም ይችል እንደነበር የገለጹት አስተያየት ሰጭያችን እንኳን ልዩ ሃይሉ የሀገርን ዳር ድንበር መጠበቅ እየቻለ የሰዎች ህይወት ሲጠፋ ግን ካምፑ ውስጥ ቁጭ ብሎ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ ቢያንስ ጥይት እንኳን መተኮስ ባይቻል አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ጉዳቱን መቀነስና መከላከል ይቻል እንደነበር አንስተዋል አስተያየታቸው የሠጡት የኮፈሌው ነዋሪ፡፡
በዛን ዕለት ከቀበሌ ሊቀ መንበር ውጭ ችግሩን ለማስቆም ጥረት ያደረገ የመንግስት አካል አለመኖሩን የገለጹት ነዋሪው ለዚህ ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው የዞንና የወረዳ አስተዳደር አካላት ስለመሆናቸው ነው የገለጹት፡፡
የኦሮሚያ ክልል በጥቀቱ ወቅት ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የፖሊስና የአስተዳደር አካላት መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በክልሉ ችግር ሲፈጠር ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ የፖሊስና የአስተዳደር አካላት ላይ ጭምር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት ቀደም ብለው ሃላፊነታቸውን በመወጣት ችግሩን መከላል እየቻሉ ነገር ግን ይህንን ያላደረጉ የዞን፣ወረዳና የከተማ አመራሮች በሕግ ቁጥጥር ሥራ ውለዋል ብለዋል፡፡
ነግርግን ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ ቢኖሩም በጸጥታ ሀይሉ ላይ በጥቅሉ ትችት ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
እስካሁንም በክልሉ 7ሺ 126 ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያነሱት አቶ ጌታቸው ገና በብጥብጡ እጃቸው ያለ እና በሕግ የሚፈለጉ መኖራውን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በአርሲ፣ባሌና በምዕራብ አርሲ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው በክልሉ የዜጎችን ሰላማዊ ኑሮ የሚበጠብጥ የትኛውም ሃይል ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው ቀደም ብሎ የቤቶች ልየታ ከተደረገ በኋላ መሆን ያነሱት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የኮፈሌው ነዋሪ እርሳቸው ቤትም ጥቃት የተፈጸመው መጽሐፍ ቅዱስና ስዕል አድኖ መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡ ይህ ሁላ ሲሆን የመንግስት አካላት ቀድመው ማወቅና ማክሸፍ ሲከሰትም ቶሎ ብሎ ለህዝብ መድረስ ይገባቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡
በሻሸመኔ ከፍተኛ ችግር የደረሰባቸውና አንድ ዓለም አቀፍ ሆቴል፣አንድ መጋዘን፣ሶስት መኪኖችና በድምሩ ከ52 ሚሊዮን በላይ ንብረት የወደመባቸው አቶ ከፍያለው ድርጊቱ አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን ተናግረው ለፌዴራልና ለክልል ይህንኑ የጉዳት መጠን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የጉዳቱ ሰለባዎች ስጋት
አቶ ከፍያለው እና ሌላው አስተያየት ሰጭ አሁን ላይ ምንም ንብረት እንዳልቀራቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ከፍያከው እንደ እርሳቸው ሁሉ የችግሩ ሰለባ ከሆኑት ጋር እየተነጋገሩ ጉዳዩን ለመንግስት አሳውቀናል ብለዋል፡፡ የኮፈሌው ነዋሪ ግን ከዚህ በኋላ በአካባቢው ብቻ ሳይሆን በዞኑም የመኖር ተስፋቸው መሟጠጡን አንስተዋል፡፡
በችግሩ ወቅት ከለበሱት ልብስ ውጭ ምንም ነገር እንዳልነበራቸው የሚያነሱት ተጎጅዎቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ የኮፈሌው ነዋሪ አሁን ከፍተኛ ስጋት እንዳለና “የክርስቲያንና የአማራ” በሚል ምዝገባ መኖሩን ለአል ዐይን ተናግዋል፡፡ ይህንንም መንግስት ቀድሞ በመከታተል ማክሸፍና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡
አሁን ላይም ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን የየከተማዎቹ ሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
ዜጎች በከፍተኛ ሥጋት ላይ ናቸው ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ጌታቸው ሕብረተሰቡ የጸጥታ መናጋት ምልክቶች ሲያይ ጥቆማ በመስጠት መንግስትን እንዲተባበር የጠየቁ ሲሆን ይህንን ለማድረግ ጥቆማውን እስከ ክልል ማድረግ እንደሚችልም ነው ያነሱት፡፡
ኃላፊው ችግር ለመፍጠር እየታሰበ ያለው በተደራጀ አኳኋን መሆኑን ገልጸው በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ግን አሁን ላይ ግን ምንም አይነት ስጋት እንዳይገባቸውና መንግስት ከጎናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያይዘ 5ሺ የሚሆኑ ሰዎች በሕግ መያዛቸውን አንስተዋል፡፡
ኃላፊው ለአል ዐይን እንደገለጹት ክስተቱን ተከትሎ መንግስት እርምጃ እየወሰደ ሲሆን አሁን ላይም ከችግሩ ጋር ግንኙነት ያላቸውና እስካሁን ያልተያዙ ሰዎች በሕግ እየተፈለጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ አካል ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል ተውጣጥቶ ወደ ቦታዎቹ ማምራቱንም አቶ ንጉሱ ገልጸዋል፡፡ወደ ሥፍራዎቹ ያቀናው ቡድን የሚያቀርበውን መረጃ በቀጣይ ለሕዝብ እንደሚገለጽ የተናገሩት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ብዙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ችግሩን ለመቆጣጠር መስራታቸውን ገልጸው ኃላፊነታቸውን ያልተወጡና በችግሩ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡