በህዳር ወደ ስራ እገባለሁ ያለው የምክክር ኮሚሽን ምን ላይ ደረሰʔ
መሠረት የመጣል ስራ ስሰራ ከርሜያለሁ ያለው ኮሚሽኑ፤ የችኮላ ስራ እንዳይሆን መጠንቀቅን መርጫለሁ ብሏል
የታጠቁ ኃይሎች በንግግር እስካመኑ ድረስ በሩ ለሁሉም ክፍት መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል
በወርሃ የካቲት 2014 ዓ.ም ተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን “መሰረት ላይ እየሰራሁ” መሆኑን ገልጿል።
ኮሚሽኑ በህዳር ሊያካሂድ ያሰበውን ሀገራዊ ምክክር “ለጥንቃቄ ስል ጊዜውን ገፍቸዋለሁ” ያለ ሲሆን፤ “የታጠቁ ኃይሎች በንግግር እስካመኑ ድረስም በሬ ክፍት ነው” ብሏል።
አል ዐይን አማርኛ ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር መላኩ ወ/ማርያም ጋር በኮሚሽኑ ጉዞና ቀጣይ ውጥን እንዲሁም በታጣቂ ኃይሎች ተሳትፎና ስጋቶች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል።
ሙሉ ቆይታው እንደሚከተለው ቀርቧል፤
አል ዐይን፤ የኮሚሽኑ መቋቋም ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረ ነው። ከተመሰረተም ስምንት ወራት ያህል ሆነውታልና የእስካሁን የኮሚሽኑ ጉዞ ምን ይመስላል?
ኮሚሽነር መላኩ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንደሚታወቀው ስራውን የጀመረው ኮሚሽነሮች በተሾሙ ማግስት ነው። ኮሚሽነሮች የተሾሙት የካቲት 2014 ዓ.ም ነው። በም/ቤት ቀርበን ቃለ መሃላ በፈጸምን በሁለተኛው ቀን ማለት ነው [ወደ ስራ የገባነው]።
[የምክክር ኮሚሽኑ] ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር ስለሆነ አንደኛ ራሳችን 11ዱ ኮሚሽነሮች የምንተዋወቅ አልነበርንም። የተወሰነ ጊዜ መውሰድ ነበረብን። ያው ይሄ ስራ በጋራ የሚሰራ በመሆኑ መግባባት መፍጠር ነበረብን። አንድ እሱ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ራሱን ማንዴታችንን [የኮሚሽኑ ስልጣንና ኃላፊነት] በደንብ ጠንቅቀን ማወቅ ነበረብን። እስሱን ለማድረግ የተወሰነ ጊዜ ወስዶብናል።
ከዚያ በኋላ ምን ምን ስራዎች እንደሚሰሩ በቤቱ እያከናወንን ቆየን። ከዛ ባሏ ወደ ስራ ገባን። የቅድመ ዝግጅት ስራ እንደሚታወቀው ጽ/ቤት ማደራጀት እና የተለያዩ ለስራችን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማደራጀት ነበረብን።
ስትራቴጅክ እቅዳችንን ማዘጋጀትም ነበረብን። የተቋሙን አደረጃጀትም እንደዚሁ በሚገባ አኩኋን በባለሙያ ማሰራት ነበረብን። ያንን ጨረስን። ከዚያ በኋላ ከባለድርሻ አካላት ጋር ብዙ ውይይቶች ነበሩን። ምክንያቱን የሀገራዊ ምክር ሂደቱ ራሱ ወሳኝ ነው። ሂደቱ በጣም ወሳይ ነውና ሂደቱ በነፃነት፣ በግልጽነትና በአሳታፊነት መከናውን ስላለበት የሚመለከታቸውን ባለድርሻዎች እያነጋገረ ቆየን። ያው ከእነሱም ጋር ቢሆን በሂደቱ መግባባት ነበረብን። በኮሚሽኑ እምነት ሊያድርባቸው ይገባል። እና ያንን ስራ ስንሰራ ቆየን። በጣም በርካታ ስራዎችን ሰርተናል እውነት ለመናገር። ይሄ [ምክክሩ] ዝም ብሎ ዘው ተብሎ የሚገባበት ጉዳይ አይደለም። ሀገራዊ ጉዳይ ነው። አይደለም ሀገራዊ ጉዳይ መስራት ቤትም መሰረቱ ላይ ነው። እና መሠረት የመጣል ስራ ነበር ስንሰራ የነበረው።
አል ዐይን፡ አብዛኛው ሰው ሲጠብቀው የነበረው ከተራ ተርታው የማህበረሰብ ክፍል ጋር መቼ ምክክሩ ይጀምራል የሚለውን ነው። ኮሚሽኑ በህዳር አጋማሽ በሀገር አቀፍ ደረጃ ውይይቱን እንደሚጀመር አሳውቆ ነበር። በተለይም አጀንዳ ለመሰብሰብና በምክክሩ ምን አይነት ጉዳዮች ይነሱ የሚለው እንደሚጀመር ሲጠበቅ ነበር።
ይሄ ውጥን ምን ሆነ? ምንስ ገጠመው?
ኮሚሽነር መላኩ፡ ይህ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት አዋጅ በጣም ጥልቅ ነው። በአዋጁ ላይ የተዘረዘሩ ነገሮች በጣም መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። አሁን ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ነገሮች አይደሉም። በወደፊት፣ በትውልድ፣ ዘመን ተሻጋሪ ነገሮችን ያካተተ ነው። እና እስከ ዛሬ የነበረበትን ሁሉ የመጣንበትን ሂደት ለመቀየር የሚያስችል እውነተኛ መሳሪያ ነው።
የሰው ጉጉት አይፈረድም። አገራችን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ነው ያለችው። ስለዚህ አንድ የሆነ ሀገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ማየት የሁሉም ፍላጎት ነው፤ የሁሉም ቀና አመለካከት ያለው ዜጋ ፍላጎት ነው። ይሄ ይታወቃል።
ግን ውስጡ ሲገባ ነው በጥንቃቄ መስራት እንዳለበት መረዳት የሚቻለው። የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግርግዳው ሰንበሊጥ ነው። እና በጥሩ መሠረት ላይ መጀመር አለበት በሚል ጊዜ ወስደናል። የዛኔ ህዳር አገማሽ ተባለው አንዳንድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቀን ወደዛ ልንገባ፤ ልንደርስ እንችላለን በሚል እሳቤ ነው። ነገር ግን ግምት ሁሌ ትክክል ይሆናል ማለት አይደለም።
በእርግጥ የገጠመን ውስጣዊ፤ ውጫዊም ሊያዘገየን የሚችል ገፊ ምክንያት አልገጠመንም። እኛ ግን የተሻለ ስራ ለመስራት ህዝቡ የሚፈልገው ነገር፤ እኛም በያንዳንዳችን የምንፈልገውን ነገር ለማየት በሚያስችል አግባብ መካሄድ አለበት ብለን ስላመንን ነው። ሌላ ምንም ገፊ ምክንያት ኖሮ አይደለም።
ትውልድ የሚሰራበት ትልቅ ትልቅ የሆነ፤ ግዙፍ ፕሮግራም ነው። በዛ መንፈስ ነው ለማለት ነው።
አል ዐይን፡ አሁን ላይ ሀገር አቀፍ ምክክሩ በጊዜያዊነት እየተባለ ያለው ጥር አካባቢ ነው። ይሄን አሁን ላይ እየተነጋገራችሁ ያላችሁት?
ኮሚሽነር መላኩ፡ ህጉ ይሄ ነገር አካታች መሆን አለበት ይላል። ይህን ደግሞ የማስፈፀም ኃላፊነት የኛ [ኮሚሽነሮቹ] ነው። አካታች እንዲሆን በአሁኑ ወቅት እያደረግን ያለነው ምንድነው፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳ እንዴት ነው የሚሰበሰበው፣ ከየት ነው የሚጀምረው፣ አጀንዳ ለማሰባሰብ የት ነው ውይይት የሚካሄደው፣ እንዴት ነው ተሳታፊዎች የሚለዩት፣ የሚለዩበት የአሰራር ሰርዓትስ ምንድነው፣ ምን መምሰለ ነው ያለበት የሚለው ነገር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በየደረጃው እየተነጋገርን ነው።
አል ዐይን፡ ልየታ (ማፒንግ) ማለት ነው?
ኮሚሽነር መላኩ፡ አዎ “ማፒንግ” ማለት ነው። እና በየቦታው እየዞርን፣ በየክልሉ ከባለድርሻዎች ጋር እየተነጋገርን ከእነሱ ደግሞ በጣም ገንቢ የሆኑ አስተያየቶችን እያገኘ ነው ያለነው። ከሁለት ክልሎች በስተቀር በአብዛኞቹ ክልሎች ይህን ሰርተናል። አዲስ አበባንና ድሬዳዋን ጨምሮ። ይህንን በሚቀጥሉት አስር ቀናት እንጨርሳለን። ምክንያቱም የባለድርሻ አካላት ይሁንታ ሊኖረው ይገባል። አሰራራችን ግልጽነት ያለው፤ አሳታፊነት ያለው መሆን ስላለበት ማለት ነው። ይሄ በቀጥታ ወደ ዋናው ውይይት የሚወስድ ነው። ስራው ከሞላ ጎደል እየተገባደደ ነው።
አል ዐይን፡ መልካም። የምክክር ኮሚሽኑ ታሪካዊ ኃላፊነትና አደራ የተጣለበት ነው። በብዙዎችም የሚጠበቅ ነው። በሀገሪቱ ያለን መከፋፈል፣ ልዩነትን በማጥበብ ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣትማ ለነገ ልጆቻችን ለምናስረክባት ሀገር መሰረትን ጥሎ ያልፋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። ነገር ግን ስጋትም አለ። በተለይም በተለያዩ ቡድኖች ለአብነትም ያህል በመንግስትና በሊሂቃን የመጠለፍ ዕድል አለው የሚል ስጋት አለና እነደዚህ ለሚሉ ወገኖች ምን አይነት መተማመኛ ትሰጣላችሁ?
ኮሚሽነር መላኩ፡ ይሄ ስጋት ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ ነው። እኛ በህጉ ላይ የተቀመውን የአካታችነት ጉዳይ ማረጋገጥ አለብን። በዚህ ሂደት አንድም የሚቀር የህብረተሰብ ክፍል አይኖርም። ምክንያቱም ይቺ ሀገር የሁላችን ናት። የተወሰኑ ግለሰቦች አደለችም። በታሪኳ ደግሞ ይሄ የመጀመሪያዋ ነው። እንዲህ አይነት ምክክሮች በየቦታው ይካሄዳሉ፤ በተለያየ ቅርጽ። ግን ይሄ ሀገራዊ ነው፤ በብሄራዊ ደረጃ። በአይነቱ የመጀመሪያው ነው። እና ይሄ ሁሉም የሚካፈልበት፣ እገሌ አዋቂ ነው እገሌ አያውቅም የሚባልበት አይደለም። ለዚች ሀገር ይበጃል የሚለውን ሀሳብ የሚያቀርብበት፤ መድረክ የማመቻቸት ኃላፊነት ደግሞ በእኛ ላይ ተጥሏል። ይህን ደግሞ የማድረግ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው።
እኛም ከዛ ማህበረሰብን ነው የወጣነው። ይቺ ሀገር የሁላችንም ናት። ሁሉም እውነተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። ሁሉም ሀሳቡን መግለጽ አለበት። የሚጣል ሀሳብ መኖር የለበትም። ሁለኩንም በእኩልነት፣ በነፃነት የሚያሳትፍ ሂደት ነው የሚሆነው። በግልጽነት የሚያሳትፍ ሂደት ነው የሚሆነው። የሚቀር አይኖርም። በማንም ደግሞ ሊጠለፍ አይችልም። የሚጠለፍበትም አግባብ የለም። እስካሁንም የገጠመን ምንም ችግር የለም።
አል ዐይን፡ እንግዲህ ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ ትልቅ ሁነት የተከሰተው የሰሜኑን ጦርነት ይገታል የተባለው የሰላም ስምምነት ነው። ለእናንተ በተለያዩ ጊዜያት ሲነሳላችሁ የነበረው ጥያቄ የታጠቁ ኃይሎች ይሳተፋሉ ወይ የሚለው ነው። እንደ ህውሓት ያሉትን ኃይሎች የማሳተፍና የማቅረብ ሀሳብ አላቸው? በዚህ ጉዳይ ላይ ኮሚሽኑ ምን ይላል?
ኮሚሽነር መላኩ፡ የሰላም ስምምነቱን ከሰይጣንና ከተከታዮቹ በስተቀር የሚቃወም ይኖራ ብዬ አላስብም። የሰውን ሰላም የማይፈልግ ብቻ ነው ሰላምን የሚጠላው። እኛም ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የሀገራችን ሰላም እንደማንኛውም ዜጋ ያሳስበናል፤ ይመለከተናል። በሰላም ስምምነቱ በጣም ደስተኘች ነን። ግን አስቻ የሆነ ከባቢ መፈጠር አለበት። የእኛን ስራ ለመስራት ምቹ ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል። አመቺ ሁኔታው ያው መንግስት በሚያደርጋቸው ጥረቶች ይስተካከላሉ ብለን እናስባለን።
በኛ በኩል በአዋጁን በተሰጠን ኃላፊነት በሀገራችን የሚገኙ ዜጎቹን ሁሉ የሚያካትት እንደመሆኑ መጠን ይሄ ይቀራል ብለን የምንለው አይኖርም። በሰላም የሚመጣን ሁሉ፤ ለምክክር የተዘጋጀውን ሁሉ በምክክር መግባባት ሊገኝ ይችላል ብሎ ለሚያምን ሁሉ ክፍት ነው። ወደኋላ የምናስቀረው ክፍል አይኖርም።
ምክክር የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ ነውና በምክክር ሂደት ሰዎች እንዲያምኑ እኛም በተለያዩ ዘዴዎች፣ እንቅስቃሴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እየሰራንም እንገኛለን፤ ወደፊትም አጠናክረን እንሄዳለን። ምክንያቱም በመጀመሪያ በምክክሩ ማመን አለብን። ምክክር አስፈላጊ ነው። በምክክሮች ነው ችግሮቻችን መፍታት የምንችለው ብሎ ማመን በጣም ወሳኝ ነዉ። ሰዎች ለምክክር ፈቃደኛ እንዲሆኑ የተቻለንን ነው ሁሉ እናደርጋለን። የማናሳትፈው ክፍል አይኖርም ማለት ነው።
አል ዐይን፡ ስለዚህ ትጥቃቸውን ፈተው በንግግርና በውይይት ሲያምኑ ብቻ በምክክሩ ሂደት የመሳተፍ ድል አላቸው ማለት ነው?
ኮሚሽነር መላኩ፡ ጠበንጃ እና ውይይት እኮ አብረው የሚሄዱ አይደሉም። ወይ ጠበንጃ ነው ወይ ውይይት ነው። በመሀል ያለም አይመስለኝም። እኛል ደግሞ የተሰጠን ኃላፊነት ሀገራዊ ምክክር እንድናዘጋጅ ነው። ምክክር ደግሞ በተፈጥሮው እንደዚህ አይነት ነገሮችን የሚያስተናግድ አይደም። በጣም ተቀራኒ የሆኑ ነገሮችን የሚያስተናግድ አይደለም። መሬት ላይ ቁጭ ብለው ሀገር ቤት፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ላይ ቁጭ ብለው የሚነጋገሩበት ነው እንጂ የሆነ መሳሪያ አስቀምጠን የምንነጋገርበት አይደለም። ስለዚህ ወደሰለጠነ አካሄድ እንሂድ ነው ጥያቄው። አዋጁም የሚለው ይሄን ነው። የእዝከ ዛሬው ይበቃናል። ብዙ ደም ፈሰሰ፣ ብዙ ህይወት ጠፋ፣ ብዙ ንብረት ወደመ፣ አገራችን እኮ የኋላ ኋላ ኋላ ሆነች። ይበቃል። እንደ ሰለጠነ ህዝብ በምክክር፣ በሀሳብ ፍጨት፣ በሀሳብ በላይነት እንመን። ምን አተረፍን? ምን ያገኛል ነገር አለ? ልጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንን፣ አባቶቻችንን ከማጣት ውጪ ምን አገኘን? እውነት ምን አገኘን? በየትኛው ነው መሻሻል ያሳየነው? በጦርነት በመገዳደል ያገኘናቸው ቱሩፋቶች ምንድን ናቸው? ምንም። ይሄ ብቻ ይብቃ ነው በአጭሩ። የአዋጁም መልዕክት ይሄ ነው።
አል ዐይን፡ እንግዲህ ማህበረሰቡ ላይ ወርዶ ይህን ማድረግ ትልቁ ፈተና የሰላምና የደህንነት እጦት ነው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰላምና ደህንነት የለም። ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ማህበረሰቡን ወርዳችሁ ማነጋገር፤ ማወያየት ከባድ አይሆንም? ለስራችሁ እንቅፋት የሚሆነው ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታን እንዴት አያችሁት?
ኮሚሽነር መላኩ፡ እውነት ነው። እንደተባለው ሰላምና መረጋጋት ባለበት ሁኔታ ነው ቁጭ ብሎ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መመካከር የሚቻለው፤ ሀሳብን ማንሸራሸር የሚቻለዉ። ይሄ ምንም የሚያነጋግር ጉዳይ አይደለም። መንግስት በዚህ ረገድ የሚሰራውን የድርሻውን ይወጣል ብለን እናስባለን። በየደረጃው ሽማግሌዎች አሉ፤ አባገዳዎች አሉ፤ የኃይማኖት አባቶች አሉ። የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እናሳስባለን። እኛም ድጋፍ የማድረግ፣የማነሳሳት ኃላፊነት አለብን። ይህንም እናደርጋለን። ምክክሩን ለማድረግ እነዚህ ሁኔታዎች መቀረፍ እንዳለባቸው ይታመናል።
አል ዐይን፡ ይህ ኮሚሽን በህወት አንዴ የሚመጣ ድል ነው። በኮሚሽነርነት ከብዙ ጥቆማና ምልመላ በኋላ የተሰየማችሁ ሰዎች ኃላፊነታችሁን የምትወጡበት መድረክ ነው። ከዚህ ሀገራዊ ምክክር ምን ውጤት ትጠብቃላችሁ?
ኮሚሽነር መላኩ፡ እስከ ዛሬ ድረስ በጣም የሚያሳዝን፣ ልብ የሚሰብር ነገር ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው። ሁሉ ነገር እያለን፣ ሁሉ ነገር ተሰጥቶን። ምድርን የሰጠን እግዚአብሔር ነው። በምድር ውስጥ ያለውን ሀብት ውሉ የሰጠን እግዚአብሔር ነው። እኛ የምንጋጭበት ነገር አንዳንዴ ቁጭ ብሎ ለአሰበው ሰው በጣም ግራ ይጋባል። እና የምክክሩ እድል ሊገኝ የሚችል አይደለም።
ብዙ ጊዜ ሲጠየቅ ነበር። “ብሄራዊ መግባባት ለዚች ሀገር ያስፈልጋል። መመካከር፣ መነጋገር አለብን” እያሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር። እውነት ነው። ጊዜው ደረሰና አዋጅ ታውጆ አንድ ተቋም እንዲቋቋም ተወሰነ። ሲመጣ ይህን እድል መጠቀም አለብን። ሁላችንም ይህን እድል መጠቀም አለብን። እኛ[ኮሚሽኑ] ብቻችንን እውነት ለመናገር የምናደርገው አይደለም። አስበንም አናውቅም።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ኃላፊነት አለበት። በቃን ማለት መቻል አለበት። የጦርነት፣ የግጭት አዙሪት፣ የደም መፋሰስ አዙሪት በቃ፣ ይበቃናል። ምንም ያገኘነው ነገር የለም። ከዓለም ኋላቀር ሆነናል። ስለዚህ ትውልዱ ራሱ መቀጠል የለብንም ማለት አለብን። በእኔ እድሜእንኳ ስንት ነው ያየሁት? ስንት ነገር ነው ያየሁት? ስንት ሰቆቃ ነው ያየነው? ከአንድ ሰብዓዊ ፍጡር የማይጠበቅ ነገር ነው ስናስተናግድ የኖርነው። በቃ ማለት መቻል አለብን።
እርግጠኛ ነኝ የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም መሮታል፣ ሰልችቶታል። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መቀጠል አይፈልግም። እየተሸማቀቀ፣ ሰላም አጥቶ፣ ለደህንነቱ ዋስትና አጥቶ የሚኖርበት ሁኔታ እንዲቀጥል አይፈልግም።
ትልቅ እገዛ እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን። ሙህራን ለማገዝ ፈቃደኞች ናቸው። በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምን እናግዛችሁ እያሉ ነው። መንግስት ራሱ በስራችን ጣልቃ ሳይገባ ምን እናግዛችሁ እያለ ነው። እንዲህ አይነት ድጋፍ ማግኘት ቀላል የሚባል አይደለም። ይህን ድጋፍ በአግባቡ ተጠቅመን በህጉ በተቀመጠው አካሄድ በስርዓት ይህን ነገር ከመራነው ሀገራዊ ምክክር፤ ሀገራዊ መግባባትን ያስከትላል ብዬ አምናለው። ሀገራዊ መግባባት ከመጣ የማንፈታው ችግር አይኖርም።
አዲስ አዲስ የሆነ ካለፈው የተለየ አይነት የሰው ልጆች መብትና ነፃነት የተከበረባት ሀገር፣ እኩልነት የተረጋገጠባት ሀገር እንደምናይ፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚያብብባት፤ የሚለመልምባት ሀገር እንደምናይ እኔ ሙሉ ተስፋ አለኝ። የገባሁትም ለዚህ ነው። ሌላ ነገር ፈልጌ አደለም። ይህን ማየት ስለምፈልግ ነው። ከዓመታት በፊት ጀምሮ ይሄ ነገር ውስጤ ስላለ ነው። ይሳካልም። ዋናው የእኛ ቁርጠኝነት ነው። በተለያዩ ችግሮች ተስፋ ሳንቆርጥ፣ የሚንገጫገጩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን ትኩረት አድገን፤ ዓላማችን ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን ከሰራን ይሳካል። የኢትዮጵያ ህዝብ በእውነት ለዚህ ትልቅ ድጋፍ ስላለው ይሳካል ብዬ አስባለሁ።
አል ዐይን፡ እንደ ኢትዮጵያ አይነት የምክክርና የእርቅ ሂደቶች በሌሎች ሀገራትም ተሞክሯል። አብዛኞቹ አልተሳካላቸውም። የተወሰኑት ደግሞ ተሳክቶላቸዋል። የዚህ አይን ተታለበት ኮሚሽን ስጋቱ ምንድን ነው? ለስራችን መሰናክል ይሆናሉ ብላችሁ የትኞቹን ጉዳዮች ለያችሁ?
ኮሚሽነር መላኩ፡ ስጋቶች ሁሌም አሉ። ስጋት የሌለበት ስራ የለም። ስጋት የሌለበት ሂደት የለም። ስጋት ተፈርቶ ግን የታሰበ ትልቅ ዓላማ እንዲያደርግ አይፈቀደም። እነዛን ስጋቶች በማስተዋል፣ በጥበብ፣ በመነጋገር እንወጣዋለን። ስጋት ከሰው ጋር የሚያያዝ ነው። በመነጋገር እንወጣዋለን እያልን ነው እንጂ ከስጋት ነፃ የሆነ ነገር አለ ማለት አይደለም። እስካሁን ግን በመጣንበት ሂደት የፈጠረ ነገር የለም። እውነት ለመናገር ጋሬጣ የሆነብን ምንም ነገር የለም።
አንዳንዶች እንደ አንድ ፕሮጀክት ነው የሚያዩት። ለእኔ ግን አይደለም። የፕሮጀክቶች ሁሉ ፕሮጀክት ነው ይሄ። የሀገር ፕሮጀክት ነው። የሁሉም ድጋፍ ስለሚኖረውም ይሳካል።
ዋናው ይጠቅማል፤ አይጠቅምም ነው። በጣም ጠቃሚ የሆነ ስራ እንደሆነ፤ ዓላማ እንደሆነ ተረድተናል። ስለዚህ ስጋቶች አይኖርም አይባልም። ስጋቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እስከዛሬ ድረስ ባለው የገጠመን ነገር የለም። እንቅፋት የሚፈጥር የገጠመን ነገር የለም። ወደፊትም አንዳንድ ነገር ቢመጣ ተነጋግረን በአግባቡ፤ በሀሳብ እያሸነፍን እንሄዳለን።