“እኔ በአንድ ነገር ገለልተኛ አይደለሁም፤ ያ አንድ ነገር ምንድነው ካልከኝ ኢትዮጵያዊነት” - ፕ/ር መስፍን አርዓያ
በቅርቡ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ፕ/ር መስፍን አርዓያ ከአል ዐይን ጋር ቆይታ አድርገዋል
“እኔ የማምነው ብሄር ከሆነ ሁላችንም ብሄር ነን፤ አለበለዚያ ሁላችን ብሄረሰብ ነን፤ አለበለዚያም ሁላችንም ህዝብ ነን ብዬ ነው” ሲሉም ነው ፕሮፌሰሩ የሚናገሩት
ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በአዋጅ ያቋቋመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ሰኞ የካቲት 14/2014 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ 11 አባላት ያሉትን የአባላትና የኮሚሽነሮች ሹመት አጽድቋል፡፡
በሹመቱ የስነ አዕምሮ ህክምና ምሁሩ ፕ/ር መስፍን አርዓያ በኮሚሽኑ ሰብሳቢነት፤ ወ/ሮ ሂሩት ገብረሥላሴ ደግሞ በምክትል ሰብሳቢነት ተመርጠው ተሾመዋል።
ሹመቱ በአብላጫ የምክር ቤቱ አባላት ድምጽ የጸደቀ ነው፤ ምንም እንኳን ድምጽ ከሰጡ 335 የምክር ቤቱ አባላቱ 5ቱ ድምጽ ከመስጠት ቢታቀቡም፡፡
ኮሚሽኑ የልዩነት ምንጭ ሆነዋል በተባና በተመረጡ አንኳር ሃገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ምክክርን ለማድረግ የሚያስችሉ መደላድሎች እንዲፈጥር በማሰብ ነው የተቋቋመው፡፡
ሆኖም ኮሚሽኑን በማቋቋሙ እና በአባላቱ የአመራረጥ ሂደት ላይ የግልጽነት እና የገለልተኛነት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች በተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር መነሳታቸው ይታወሳል፡፡
አል ዐይን አማርኛም እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን ለማንሳት ከኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕ/ር መስፍን አርዓያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡ አብረውን ይዝለቁ፡፡
አል ዐይን፡ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ሆነው በመመረጥዎ ምን ተሰማዎ?
ፕ/ር መስፍን፡ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡ ሰሞኑን ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ በህዝብ ጥቆማ 640 ገደማ ሰዎች ተጠቁመው ከዛ ውስጥ ወደ 72፣42 እያለ በስተመጨረሻ 11 ሰዎች በኮሚሽነርነት ተሰይመናል፡፡ ከአስራ አንዳችን ዘጠኛችን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተን ቃለ መሃላ ፈጽመናል፡፡ እኔም ዋና ኮሚሽነር ሆኜ ተሰይሜያለሁ፡፡ ይሄ ትልቅ ህዝባዊ ሃገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡ 120 ሚሊዮን ህዝብ የሰጠኝ ኃላፊነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ያ ማለት እኔን የግድ ያልመረጠ ያልጠቆመ ሁሉ አይመለከተውም ማለት አይደለም፡፡ ኃላፊነቴም ትክክል በአግባቡ በገለልተኝነት በተለይም በሚዛናዊነት ለመወጣት ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል፤ ይሄ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ምክንያቱም የምንነጋገረው ያለው ከ150 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ያሉ ከአንድነታችን ይልቅ ለልዩነታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮችን ነቅሶ አውጥቶ ያንን እንደገና ወደ ህዝብ አምጥቶ ህዝባችን በሚገባ ተወያይቶበት ወደ መግባባት እንዲመጣና ከዚያም በኋላ በተቻለ መጠን እርቅ ፈጥሮ ሃገራችን ወደፊት እንድትሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ስራ በጣም ከባድ ስለሆነ ድብልቅ ስሜት ነው ያደረብኝ፡፡ ምንም እንኳን እኔ የምሰራው ባይሆንም የእኔ ስራ ወይም የኮሚሽነሮቹ ስራ ሁኔታዎችን በሚገባ ማንንም ሳይለዩ ከላይ እስከታች ከጎን ወደ ጎን፣ ከምዕራብ ምስራቅ፣ ከሰሜን ደቡብ ያሉትን ህዝቦቻችንን ማቀራረብ እና ውሳኔው የህዝቦች ቢሆንም ሜዳ ማመቻቸቱ ቀላል እንደማይሆን በመገመት እንዳልኩህ ይሄን ኃላፊነት ስሸከም በጣም ክብደቱ ይሰማኛል፡፡
አል ዐይን፡ ከአሁን ቀደም በተለይ ከጦርነቱ በፊት የተለያዩ የሰላምና የእርቅ ጥረቶችን ሲያደርጉ ነበርና አሁን ያንን ጥረት የሚያሳኩበትን እድል እንዳገኙ ያስባሉ?
ፕ/ር መስፍን፡ እኔ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ከአሁን በፊት መቼም ሃገራችን የኖረችው በሃይማኖት አባቶች፣ በሃይማኖት መሪዎች እና በሃገር ሽማግሌዎች ነው፡፡ መንግስታት ይቀያየራሉ፡፡ በእኔ እድሜ እንኳን በትንሹ ሶስት መንግስታት ሲቀያየሩ አይቻለሁ፡፡ ሰዎች እንሞታለን ህዝብ ግን ይኖራል፤ ምናልባት ስያሜዋ እንደየቦታው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር አገርም ትኖራለች፤ የትም አትሄድም፤ ፈጣሪ እንዲያው እዛው ቦታ እንድትሆን እስከፈቀደላት ድረስ፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ የሃገር ሽማግሌዎች መድረክ ወስጥም ሰብሳቢ ሆኜ ከትልልቅ የሃገር ሽማግሌዎች ጋር ከእነሱ እየተማርኩ በአብሮነት በተለይም ደግሞ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት መሪዎች አባቶች ጋር በመሆን በሃገራችን ሰላም እንዲሰፍን ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ በተወሰነ ደረጃም ሰርተው ነበረ፡፡ ስኬታማ መሆን አይደለም ዋናው ትልቁ ነገር፤ ህዝባችን ምን ይፈልጋል? ነው፡፡ ህዝባችን ሰላም ጠምቶታል፣ ጦርነት አድክሞታል፣ ርሃብ አድቅቆታል፤ መሰደድ ጎድቶታል፡፡ መሰደድ ስል በሃገር ውስጥ ብቻ ያለውን አይደለም ከሃገር ውስጥ መውጣቱን፣ በበረሃ፣ በአንበሳ መበላቱንም ጭምር ነውና የምናገረው፤ ይሄ ሁሉ ነገር ምሬት ውስጥ ነው ያለነው፡፡ 75 በመቶ የሚሆነው ወጣት ህዝባችንና ህጻናት ትምህርት ቤት መሄድ፣ መማር እና ማደግ ተምረውም ስራ ማግኘት ለሃገራቸውም ልማት ላይ መዋል አለባቸው፡፡ እና ሁልጊዜ እንደምንለው ሀገራችን ባለ ብዙ ወንዞች፣ በቂ አፈር፣ በቂ መሬት፣ በቂ የሰው ኃይል እያላት አሁንም እንዳንጋጠጥን ነው ያለነው ወደ እርዳታ ሰጪዎች፡፡ አሁንም እንደ ተራብን፣ አሁንም እንደ ተፈናቀልን ነው ያለነውና እነኚህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው እንዲያው በቃን የምንልበት ደረጃ ላይ ስለደረስን ተሸንፈን የምናሸንፍበት ደረጃ ላይ መድረስ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡ መቼም ሁላችንም አሸናፊ እንሁን ካልን ማናችንም አናሸንፍም፡፡ ሁላችንም ግን ተሸናፊ ሆነን ማሸነፍ ግን እንችላለን ብዬ አምናለሁና ወደዛ የምንመጣ ከሆነ ስኬቱ የአንድ ኮሚሽነር ወይም የ11 ኮሚሽነሮች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል ብዬ አስባለሁና ተስፋዬ እዛ ላይ ነው፡፡
አል ዐይን፡ ብሄራዊ ምክክሩ በቃ ወደሚባልበት ደረጃ ያደርሰናል ብለው ያስባሉ? ኮሚሽኑስ በዛ ደረጃ ሊያሻግረን ይችላል?
ፕ/ር መስፍን፡ አስባለሁ፤ ሁላችንም ከተባበርን፤ ምንተባበረው ብዙ ነን፤ ከዚህም ወጣቶች አንዱ ናቸው፤ ከእንግዲህ ወጣት በጦርነት መማገድ የለበትም፤ ያለፈው ሊበቃን ይገባል፡፡ ብዙ ‘ክሬም’ የሆኑ ለዚህች ሃገር ሊያገለግሉ የሚችሉ ወጣቶችን በ60ዎቹ አጥተናል፡፡ በርዕዮተ ዓለም ተከፋፍለን በዛኛው ስርዓት ውስጥ ብዙ ወጣቶችን አጥተናል፡፡
በዚህኛው ስርዓትም ወጣቶች ተምረው ትልቅ ደረጃ ደርሰው ሀገርን ያስጠራሉ ብለን በምንጠብቅበት ሰዓት ወደ ሌላ የእስር በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብተን እየተጫረስን ነው ያለነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ሄደው ሄደው አሁን በቃ የምንልበት ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ አሁን በቃ የሚባልበት ሰዓት ላይ ስለደረስን፤ ወጣቱ ነገ የምረከባት ኢትዮጵያ እንዲህ መሆን፤ በዚህ መቀጠል የለባትም ብሎ ማሰብ ላይ መድረስ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አረጋውያንም እንደዚሁ፡፡ መቼም ትልልቅ ቦታ ያላቸው የህብረተሰብ መሪዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ህዝብ እንደጎርፍ ነው፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት አንድ የነቃ መሪ ከአንዱ አካባቢ ብቅ ቢልና እንዲህ ነው ቢል ብዙ ህዝብ ሊከተለው ይችላል፡፡ መዘዙ በሁሉም በዕምነቱ፣ በሃይማኖቱም፣ በፖለቲካውም ነው የሚከተለው፡፡ እና እነዚህ በተለይ የህብረተሰብ መሪዎች እነሱም ራሳቸው በቃ ሰላማዊ ህብረተሰብ መምራት ይገባናል፤ ከጦርነት መላቀቅ አለበት ብለው መነሳት አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ይሄ ሁለተኛው ነው፡፡
ሶስተኛው የፖለቲካ መሪዎቻችን ናቸው፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ተፎካካሪም እንበላቸው ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በራሳቸው ህዝባቸውንና ሃገራቸውን አንድ ደረጃ ላይ ማድረስ ይፈልጋሉ፡፡ ተሸፋ የማደርገው መልካም ነገር ላይ ነው ብዬ ነው የማስበው አካሄዳቸው አካሄዳቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህም የፖለቲካ መሪዎች አካሄዳችን እንዴት ነው፣ ለየትኛው ነው ቅድሚያ መስጠት ያለብን፣ ለጉልበት ወይስ ተሸንፎ ለማሸነፍ፣ እንዲሁም ለሰላማዊ ሂደት ነው በሚል እነሱም ወደ መሃል መምጣት አለባቸው ብዬ አስባለሁ መንግስትን ጨምሮ ማለት ነው፡፡
መንግስት አይ የለም ህዝብ መርጦኛል፣ አራት ዓመት ይቀረኛል፤ ስለዚህ ይቺን አራት ዓመት ማንም የሚነካብኝ የለም ቢል አሁንም የጎደፈ ሰላም እና የዳሸቀ ኢኮኖሚን ይዞ ልማትን ማምጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት መሪዎችም እንደዚሁ፤ መግባባቱ ሁሉም ጋር ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሃይማኖት ውስጥ፣ ወጣትነት ውስጥ ፣ ሴትነት ውስጥ፣ አካል ጉዳተኝነት ውስጥኢትዮጵያ በምትባለው ጥላ ስር ባለነው በሁላችንም ጋር ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ያስተዋልነው ነገር ስላለ፡፡
ስለዚህ የጋራ ወገንተኝት ፈጥረን የምንሰራ ከሆነ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የጠቀስኳቸውና ያልጠቀስኳቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሌሎች በሰላም እንድንኖር የሚሹ፣ የኛን ልማት፣ ከ5 ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን ያንን የሚናፍቁ ጭምር የዚህ ታሪካዊ ሂደት ዋና ተዋናይ መሆን ይገባቸዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠራው ግዛት በሙሉ የትልልቅ ታሪኮች ባለሀብት ነው፤ ምናልባት ልዩነቱ በመመዝገብ እና ባለመመዝገብ፤ ተመዝግቦ ደግሞ ወደ ውጪ ሄዶ እንደገና በሚገባ ተመዝግቦ መመለስ እና አለመመለስ መካካል ያለ ካልሆነ ሁላችንም ባለታሪኮች ነን፡፡
ስለዚህ የዚህ ሁሉ የጥንት ታሪክ ባለቤት መሆናችንን ተገንዝበን፤ የአንዳችን ባህል ከአንዳችን እንደማይበልጥ በሚገባ ተመልክተን ወደ ውይይት እናመጣዋለን። ከዛ ውስጥ እየነቀስን ደግሞ ያግባቡንን እያጣመርን ያላግባቡንን እየነቀሰን እያወጣን እየተወያየንባቸው ወደ መግባባት ከመድረስ በስተቀር ሌላ አማራጭ ያለን አይመስለኝም።
አል ዐይን፡ ኮሚሽኑን በማቋቋም እንዲሁም ኮሚሽነሮችን በመምረጥ ሂደት የግልጸኝነት እና የገለልተኛነት ጥያቄዎች ይነሳሉና ምን ይላሉ? እርሶስ እንዴት ነው የተመረጡት?
ፕ/ር መስፍን፡ እኔ የተመረጥኩት ጠቁሙ እንደተባ ሰምቻለሁ፤ እከታተል ነበር፡፡ 640 ዎቹ ውስጥ መግባቴን አላውቅም ነበር በርግጥ፡ ጓደኞቼ ብትገባ ጥሩ ነው ሲሉኝ ነበር፡፡ ግን እኔ አላማየ ጡረታየን አስከብሬ መጸኃፍ አነባለሁ የሚል ነበር፡፡ የአእምሮ ሀኪም ነኝ በዚያ ዙሪያ ብጽፍስ እንዲህ እንዲህ እምመኛቸው ስራዎች ነበሩ፡፡ ራሴን እያዘጋጀሁ የነበረው ለዚያ ነው፡፡ ትንሽ መጻህፍት ቤት ለራሴም አዘጋጅቼ፤ እየገፋ ሲሄድ አንተ ሳትመረጥ አትቀርም ብለው ወዳጆቼ ይነግሩኝ ጀመር፡፡ ጥቆማ ውስጥ ማለቴ ነው፡፡ በኋላ ግን ከተጠቆሙት 42 ሰዎች ወስጥ መኖሬን ሰዎች ነገሩኝ፡፡ እንዲያውም ከዚያ በፊት ሌላ ሊስት/ዝረዝር ነበር ይመስለኛል፤ እሱን ልከውልኝ እውነት ለመናገር ደስ ብሎኝ ነበር፤ ምክንያቱም ሊስት ውስጥ አልነበርኩም፡፡ ስለዚህ ጎሽ እንግዲህ እግዚአብሄር ነው የፈቀደው እንደተባለው መጻህፍት እንዳነብና ሌላ ሌላ የተመኘሁትን እንዳደርግ ነው በሚል እያለሁ፤ የ41ቱ ዝርዝር ደሞ ደረሰኝ፡፡ ምናልባት የ42ቱ ዝርዝርም ለ22ቱ ይሆናል ስል ነበር፡፡ 42ቱ እያፈጠጠ መጣና 11ዱ ወስጥ መግባቴ ተነገረኝ፡፡
እንግዲህ ይህን ኃላፊነት ወስዶ ስራውን ያስኬደው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጽ/ቤት፤ሂደቱ እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ ገለልተኛ ላልከው፤ እኔ በአንድ ነገር ገለልተኛ አይደለሁም፣ በተቀረ ግን ገለልተኛ ነኝ፡፡ ያ አንድ ነገር ምንድነው ካልከኝ ኢትዮጵያዊነት፡፡ ምክንያቱም እኔ ያለችኝ አንድ ሀገር ነች፤ ሌላ ዜግነት የለኝም፡፡ሌላ ሀገር አልሄድም በዚህ እድሜየ፡፡ ብሄድ ኖሬ የዛሬ 40 አመት እድል ነበረኝ፡፡ እህቶቼ እና ወንድሞቼ ወዳሉበት ሀገር ሄጄ በሃኪምነቴ የተሻለ ኑሮ መኖር እችል ነበር ብየ አሳባለሁ፡፡ እዚህ በመኖሬ ግን እጅግ የበለጠ ኑሮ ነው የኖርኩት፡፡ ለምን በሀኪምነቴ ትግራይ፣ ወሎ ሰርቻለሁ፡፡ ከዛ መጥቼ ደግሞ እዚህ አማኑኤል ሆስፒታል ዳይሬክተር ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ የአእምሮ ሀኪም ሆኜ ሰርቻለሁ፤ ቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ስርቻሁ፤ ዘውዲቱ ሆስፒታል በየቦታው በሙያየ ሰርቻለሁ፡፡ እኔን ገለልተኛ እንድሆን የሚያደርገኝ አንድ ነገር አለ፡፡ ሰው ሰው ነው፡፡ ሀኪም ስሆን ቃለመሀላ የፈጸምኩት በሰውነቱ እንዳግዝ፣ እንዳክም ምንም አይነት ጉዳት በሰው ላይ እንዳላደርስ ነው፤ በሂፖክራተስ ኦውዝ/ቃለ መሃላ፡፡ በህክምና ሙያዬ ያገኘሁትን ሚስጥር ያለታካሚው ፈቃድ ወደ ሌላ ሰው እንዳላሳልፍ እና በትክክል ያን ሰው እንድረዳ በእግዚአብሄር ሃይል ቃለ መሃላ ፈጽሚያለሁ፡፡
ስለዚህ እኔ ከዚህ ጎሳ ነው ከዛ ወንዝ ነው ነጭ ነው ጥቁር ነው ቢጫ ነው ሳልል ሰውን የማከም ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ይሄ ቅድሚያ ለሰው እንድሰጥ ያደርገኛል፡፡ ስለዚህ ፍጹም ገለልተና ነኝ ብየ አስባለሁ፡፡ ነገርግን ቅድም በነገርኩህ ምክንያት ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ ሌላ ሀገር አማራጭ ስለሌለኝ ምንም የምለው ነገር የለም፡፡ ለኢትዮጵያ የቅድሚያ ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ ያም ሰለሆነ ነው ይህንን ኃላፊነት የወሰድኩት፡፡
እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የማምነው የኤርቦሬ ጎሳ ይሁን ህዝብ ይሁን ወይም ብሄረስብ ይሁን ብሄር ይሁን፤ ምክንያቱም በዚህ ስታሊስታዊ ፍልስፍና ሰዎችን በሶስት ከፍሏቸዋል፡፡ እኔ የማውቀው ዘር ነው፡፡ ሰው አለ፤ ከዛ ውስጥ አምስት የሚሆኑ ዝርያዎች አሉ፡፡ የጥቁር ዘር አንድ ነው፤ በዛ ዘር ውስጥ ነው ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ የነጭ አለ፤ የቢጫ አለ ሞንጎሎይድ የሚባለው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዘራችን አንድ ነው፡፡ በስታሊኒስት ፍልስፍና ብሄርብሄረሰቦች እንባላለን፡፡ እኔ የማምነው ብሄር ከሆነ ሁላችንም ብሄር ነን፤ አለበለዚያ ሁላችን ብሄረሰብ ነን፤ አለበለዚያ ሁላችንም ህዝብ ነን ብዬ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሚባለው ውስጥ ሶስት ነን ብየ አላስብም፡፡ ለምን ኤርቦሬ ወይም ትንሽ የህዝብ ብዛት ያለው ህዝብ መባል፤ ትንሽ ከፍ ያለው ብሄረሰብ መባል፣ ትልቁ ደግሞ ብሄር መባል አለበት ብየ አላስብም፡፡ ይሄ የራሴ እምምት ነው ትክክል ላልሆን እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም በሶሺያሊስት ፍልስፍና ውስጥ አልፌበታለሁ፡፡ ተምሬያለሁ ግን የራሴ እምነት ነው፡፡ እና እንዳልኩህ የኔ ገለልተኝነት በሰውነት ጭራሽ ገለልተኛ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ኢትዮጵያዊነት ከሆነ ገለልተኛ ነኝ፡፡
ነገርግን ገለልተኛ የማያደርገኝ ኢትዮጵያ ከሚለው ወጣ ማለት አለብህ ከተባልኩ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ሙያየ ሀኪም መሆኔ ቃለ መሃላ መፈጸሜ፤ ይህንንም ቃለ መሃላ ደግሞ ላለፉት 40 አመታት ፈጽሚያለሁ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምናልባት አንዳንዴ ሰው ሰው ነውና በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ወደ አንዱ ካለጋደልሁ በስተቀር፡፡
አል ዐይን፡ በኮሚሽኑ የማቋቋም ሂደት ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ምን ያህል ገለልተኛ ሆኖ ሊሰራ ይችላል፤ በተለያዩ አካላት ጫና ውስጥ ላለመግባቱስ ምን ዋስትና የሚል ጥያቄንም ያነሳሉና ምን ይላሉ?
ፕ/ር መስፍን፡ እንደኔ እምነት መራጭ ባልሆንም ገለልተኛ በሆነ ሂደት ተመርጫለሁኝ ብየ ነው የማስበው፡፡ ሌላው በማንነት ኮሚሽን ውስጥ ነበርኩ፡፡ እዛ ሳለሁ የተማርኩት ብዙ ነገር አለ፡፡ በኮሚሽኑ ውስጥ የነበሩ ሰዎች እንደ ኦፌኮ፣ኢዜማ፣አብን እና ትዴፓ ከመሳሰሰሉ ፓርቲዎች የተውጣጡ ታላላቅ አመራሮች እንዲሁም ምሁራንና የቀድሞ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡ በእኔ እምነት በኮሚሽኑ የተሰጠንን ኃላፊነት ዓላማ በጋራ ተወጥተናል ብየ አስባለሁ፡፡ እኔ ከዚህ ፓርቲ ነው የመጣሁት የእኔ ብቻ ይሰማ ሳይባል በተቻለ መጠን በጋራ ነው የተወጣነው፡፡ እኔ እንግዲህ የትኛውም ፓርቲ ውስጥ ስላልነበርኩ ያስተዋልኩትን ነው፤ በመከባበር ነው ሶስቱን ዓመታት ያሳለፍነው፡፡
ይህ ኮሚሽን ደግሞ የተሰጠው ኃላፊነት ከዛ የተለየ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ገለልተኛ ሆኖ ያለምንም ልዩነት ሁሉንም አካታች ሆኖ ሁሉንም ወገኖች የህጻናትንም ተወካዮች ሳይቀር ወደ ጠረጴዛ አምጥቶ በማወያየት አንድ ደረጃ ላይ ማድረስ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ እንዳልኩህ ገለልተኝነት ሳይሆን ሚዛናዊነት ብለው ይሻላል፡፡ ይኸ ሚዛናዊነት ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ገና መጀመራችን አሁን እየተናገርኩ ያለሁት ስለ ራሴ ስለ ዋና ኮሚሽነርነቴ ነው እንጂ ሁላችንም ሁሉን ነገር ካብላላን በኋላ አንድ ተናጋሪ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስራችንን በየጊዜው ለህዝብ ስናቀርብና ስናሳውቅ ምን ያህል ገለልተኛ ምን ያህል ሚዛናዊ እንደሆነ ይታያል፡፡
አል ዐይን ፡ ልክ ዛሬ እንደሰማነው የወሰንና ማንነት እንዲሁም የእርቀ ሰላም ኮሚሽንን ዐይነት የመፍረስ እጣ ፋንታ እንዳይገጥመው ምን ዋስትና አለው በሚሉ የሚሰጉ አሉ፡፡ ስለዚህስ ምን ይላሉ?
ፕ/ር መስፍን ፡ በእ/ሔር ፈቃድ ጠንክረን እንሰራለን፤ ግልጽ ሆነን እንገኛለን ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንደሚሰማኝ ሁሉም ህዝብ ከእኛ ጀርባ ነው ብየ አስባለሁ፡፡ ህዝቡ እያሰበ እየጸለየልን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ጦርነት ያልታከተው የለም፣ አሁን እኔ እና አንተ በምንነጋገርበት ሰአት ወገኖች በጦርነት ላይ ናቸው እንዲሁም በየጫካው እየተራቡ፣ ታርዘውነው ያሉት፡፡ እናቶች በየቦታው ካለረዳት እየወለዱ ነው ያሉት፡፡ ይህ ሁሉ በምናይበት ጊዜ በጣም እርግጠኛ ነኝ ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ ከኛ ጀርባ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፤ በትክክል ዓላማውን እስከተረዳ ድረስ፡፡ ይህን የማይፈልጉ ጥቂቶች ደግሞ ሊኖሩ ይችላሉ፤ በመረዳት ወይም ባለመረዳት፡፡ ይሄ ደግሞ ማለት አይደለም ያለ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው አንዱ አንድ ቢያስብ ሌላኛው ሌላ ሊያስብ ይችላል፡፡ ሌላው የሚያስበው ግን አካሄዱ የተሻለ ነው ብሎ ባሰበበት መንገድ እንጂ ለሃገሩ ጥፋት የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡
አል ዐይን ፡ አሁን ጦርነት ውስጥ ነው ያለነው፤ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ ጽንፍ የያዙ አስተሳሰቦች ባሉበት ሁኔታም ነው ኮሚሽኑ የተቋቋመውና እነዚህ ሁኔታዎች ምን ዐይነት ተግዳሮትን ለእናንተ ሊደቅኑ ይችላሉ? እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ለመስራትስ ይቻላል ወይ?
ፕ/ር መስፍን፡ ባንድ ወቅት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያገር ሽማግሌዎች ሄደን ነበር፡፡ እዚያም ላይ እኔ እናገር ነበር፡፡ ከመሄዴ በፊትም ስለ ህዝቡ ስብጥር አውቅ ነበር፡፡ የትኛው ነው ከመሃል አገር ፖለቲካ፣ ከትምህርት የራቀው እያልኩ እጠይቅ ነበር፡፡ ይሄን ቅዱስ ጳውሎስ ሳስተምር አውቃቸው የነበሩ ከክልሉ የሚመጡ ብዙ ተማሪዎች ይነግሩኛል፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የትኛው ነው እድል ያገኘው፣ ያልደረሳቸው ምንድን ነው የሚለውን ስናይ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ የህዝባችን አኗኗር እና ጥያቄ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ ለምንድን ነው ህዝባችን በየቦታው ተቧድኖ እርስ በርሱ የሚጫረሰው? እነዚህን መሰረት በማድረግ ጥያቄዎቻቸውን ለማስመለስ የትጥቅ ትግልን ጨምሮ የተለያዩ የትግል ስልቶችን ያነሱ አካላት በየክልሉ ይኖራሉ፡፡ እንደምናውቀው ጠመንጃ መያዝ የሚመጣው ከብሶት ነው፡፡ ከጠመንጃ መያዝ ጋር ስልጣን ይመጣል፤ ብዙ ነገሮችም ይኖራሉ፡፡ የውጭ ተጽዕኖዎችም ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ወደ ውጭ ከማየታችን በፊት የራሳችንን የቤት ስራ መጨረስ አለብን፡፡ ይሄ በውይይት ነው የሚመጣው፡፡ ለአፋሩም፣ ለጉሙዙም፣ ለኮንሶውም ሆነ ለሌላው ያሉባቸው ችግሮች የሚፈቱት በውይይት ነው፡፡ ውይይት የሚባለው ነገር ወደዛ ያመጣናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አል ዐይን፡ የኮሚሽኑ አጀንዳዎች በማን ነው የሚቀረጹት? የመጀመሪያው ስራችሁስ ምንድን ነው?
ፕ/ር መስፍን፡ የመጀመሪያው ስራችን 11ዱ የኮሚሽኑ አባላት እርስበርስ መተዋወቅ ነው፡፡ መተዋወቅ ከስም ይዘላል፡፡ በመቀጠል እያንዳንዳችን ምን ይዘን መጣን አስተዋጿችን ምንድን ነው የሚለውን እናያለን ከዚያም ውይይት ነው ወይስ ድርድር ነው የሚለውን እናያለን፡፡ በመጀመሪያ የምክክር ኮሚሽን አዋጅን ጽንሰ ሃሳቦቹን በሚገባ መረዳት ነው፡፡ አባላቱ አብዛኞቹ ጥሩ የህግ ልምዶች አሏቸው፡፡ ከእድሜ እና ከስራ ልምዳቸው አንጻር ሲታይ ስብስቡ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ የራሳችንን የስራ መመሪያ ወይም ኮድ ኦፍ ኮንዳክት እናወጣለን፡፡ ይሄን እያወጣን ነው፡፡ በፓርላማ ማጸደቅ ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ስራዎች ከገመትኩት በላይ በዚህ ሶስትና አራት ቀናት ውስጥ ተሰርተዋል፤ እየተሰሩ ይሄዳሉ፡፡ በእኛ ጥንቅር በዛ ያሉ የህግ አዋቂዎች የካበተ ልምድ ያላቸው ወጣቶችም ሴቶችም አሉ፤ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡
በሀገራዊ ምክክሩ ሊነሱ የሚችሉት አጀንዳዎች የትኞቹ ሊሆኑ ይችላሉ?
አል- ዐይን፡ ለምክክር የሚሆኑ መደላድሎችን በመፍጠሩ ሂደት ለሃገር በቀል እውቀቶች ወይስ ከተለያዩ የውጭ ሃገራት ለሚገኙ ልምድና ተሞክሮዎች ነው ቅድሚያ የምትሰጡት?
ፕ/ር መስፍን፡ እንግዲህ የእኔን የግል ሃሳብ ነው የምትጠይቀኝ፤ ምክንያቱም አንተ የምትለውን ነገር ወደፊት የምናብላላው ነው፡፡ እኔ የሀገር ሽማግሌዎች መድረክ ውስጥ እያለሁ የተማርኩት ነገር እዛ ሰብሳቢ ሆኘ እዚህ አዲስ አበባ ነው ቁጭ ያልኩት፤ ሌሎች ትልልቅ ሰዎች እዛ ቦርድ ውስጥ አሉ፤ ነገር ግን ትልቅ ትምህርት ያገኘነው ከአካባቢ፤ የሀገራዊ ሽማግሌዎች ነው ፡፡
የሚገርም ዕውቀት ያልተጠቀምንበት በየቦታው ያለ ሽምግልና አለ፤ በየቦታው የሀገራችን ገራዶች፤ ኡጋዞች፣ ሱልጣኖች፣ አባገዳዎች በየቦታው ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች ከአማራ፣ ከትግራይ፣ከኦሮሚያ የሚመጡ አባገዳዎች፤ ከደቡብ የሚመጡ ታአምር ነው፤ ከሱማሌ፣ ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚመጡ ሽማግሌዎች ማለት ከሁሉም ክልሎች ለማለት ነው፤ ከሀረር የጥንት ዕውቀት ያላቸው ሽማግሌዎችን እንዲያው አንድ ሰዓት፤ ሁለት ሰዓት ሰጥተህ ብታዳምጣቸው የሚገርም ዕውቀት አላቸው፤ የሚገርም የግጭት አፈታት ዕውቀት አላቸው፤ የሚገርም የመደማመጥ ዕውቀት አላቸው፡፡
እኛ አሁን “ዘመነኛ” የምንባል ሰዎች ችግራችን አናዳምጥም፤ እንናገራለን ብዙ መጽሃፎች እናጣቅሳለን፡፡ ክላሲካል የሆነውን የፍልስፍና መጽሃፍ ጀምረን እስከብዙ ነገር ግን እናጣቅሳለን ጓዳ ያለውን ዕውቀት ግን አናውቀውም፡፡ እኛ ብዙ የምናውቀው የአውሮፓውን ወይም የእስያውን አሊያም የመሳሰለውን ነው፤ እዚሁ እኛው ሀገር ውስጥ ብዙ ተሞክሮ አለ፡፡ እና እኔ እንዲያው የምመኘው የሀገር ውስጥ፤ የውጭው ተሞክሮ የሚናቀው አይደለም፤ በዚህ እኛ በምንሰራው አይነት ስራ ዙሪያ ሰርተው የተዋጣላቸው አሉ፤ ያልተዋጣላቸውም አሉ የነሱንም ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ ግን ሀገር ውስጥ የተደበቀውን የሀገር ሽምግልና የሃይማኖት መሪዎች ዕውቀት ብታየው ጉድ ነው የሚያሰኘው እና እኔ መቸም እንዳልኩህ በጣም ትልልቅ ዕውቀት ያላቸው በዚህ በግጭት አፈታት ላይ በዓለም ደረጃ ያሉ ኢትዮጵያውያን አሉ እሰየው ነው፤ እነሱን እንጠቀማለን፡፡ ያማለት ግን የሀገርኛ ዕውቀት ወደፊት አይመጣም ማለት አይደለም፤ ምናልባት እሱ እንዲመራ ነው የኔ ምኞት ብዬ አስባለሁ፡፡
አል- ዐይን፡ ገለልተኛነቱን ጨምሮ ‘ገና ከጅምሩ ከሽፏል’ የሚሉ አንዳንድ አካላት እንዳሉ ቀደም ሲልም ከገለልተኛነቱ ጋር በተያያዘ አንስቻለሁና ቀረ የሚሉት ነገር ካለ እድሉን ልስጥዎት?
ፕ/ር መስፍን፡ እኛ ገና ስራ መጀመራችን ነው፤ በእርግጥ ይሄ ከሽፏል የሚለው ነገር እንግዲህ እንዳነሳስህ ነው፤ አንድ ሯጭ መጀመሪያውኑ ይህንን ጨዋታ አላሸንፈውም ካለ ወይም ሮጨ አልጨርስም ካለ አይጨርስም፡፡ ስለዚህ አንድ ሯጭ መጀመሪያ ሲነሳ (ሻለቃ ኃይሌ እዚህ ጎረቤትህ ነው እንዴት ነው የምትነሳው ብትለው) ምን ያደርጋል? መጀመሪያ ሲነሳ ሪከርደን አሻሽላለሁ ብሎ ነው የሚነሳው አሸንፋለሁም ብሎ አይደለም፤ ስለዚህ እኛ ከሽፈናል ብለን አንነሳም፡፡
እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተቻለ መጠን ኃላፊነቱን ወስዶ ሕዝብ መርጦናል፤ ስለዚህ በተቻለ መጠን ውጤታማ መሆን አለብን ብለን ነው የምንነሳው፡፡ እኛ አይደለንም እሆናለን የምንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ውጤታማ ይሆናል ብለን ነው የምስበው፡፡ ስለዚህ 100 ምናምን ሚሊዮን ሕዝብ ከጀርባችን ከሆነ ለእኛ አይደለም እንዳው እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሆነ ለቀጠናው፣ ለአህጉሩም ተምሳሌታዊ የሆነ አካሄድ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ ዓላማችን ሌሎቹንም ከጎረቤት ያሉትን ያኮረፉ ወንድሞቻችንን ቀስ በቀስ ወደመግባባቱ መድረክ እናመጣቸዋለን ነው፡፡ ይሄ ኤርትራን ሊጨምር ይችላል፤ ጅቡቲን ሊጨምር ይችላል፤ ሶማሊያ ላንድን፣ ሶማሊያን፣ ኬንያን፣ ደቡብ ሱዳንን ፤ ሱዳንን እነኝህን ብንጨምር ደግሞ ታላቅ ሀገር እንሆናለን፡፡ ታላቅ ሀገር ወይም ታላቅ አህጉር መሆን እኔ እንደምናገረው ቀላል አይደለም፤ ብዙ መስዋዕትነትን፤ ብዙ ድካምን ፤የመሪዎቻችንን ብልህነትና ጥበብ ይጠይቃል፤ እንግዲህ ለዚህ ሁላችንንም እኛንም ጨምሮ እግዚአብሔር ይርዳን ነው የምለው፡፡
አል ዐይን፡ እናመሰግናለን፡፡
ፕ/ር መስፍን፡ እኔም አመሰግናለሁ፡፡