ባለሙያዎቹ የ“ህገመንግስት ትርጉም” መስጠትን የሚደግፍ ሀሳብ አቀረቡ
ምርጫ ተራዝሞ “ህገመንግስታዊ ትርጉም” አንዲሰጥ በተወካዮች ምክርቤት መጽደቁ ይታወሳል
ባለሙያዎች የህገመንግስት ትርጉም መስጠት አስፈላጊ ነው ያሉበትን ምክንያት አቅርበዋል
ባለሙያዎች የህገመንግስት ትርጉም መስጠት አስፈላጊ ነው ያሉበትን ምክንያት አቅርበዋል
የህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በዛሬው እለት ባዘጋጀው መድረክ ኢትዮጵያውያን የህገመንግስት ባለሙያዎች በቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡
የአጣሪ ጉባኤው ሰብሳቢና የጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዘዳንት መአዛ አሸናፊ መድረኩን የመሩ ሲሆን እሳቸውና ሌሎች የጉባኤው አባለት ለአቅራቢዎቹ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡
ጉዳዩን የማየት ጀምሬያሉሁ ያለው ጉባኤው የህገመንግስት ባለሙያዎችና የህግ ባለሙያዎች ሲሰማ ውለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የህገመንግስት ባለሙያዎች የየራሳቸውን ምልከታ አጋርተዋል፡፡
ባለሙያዎቹ የህገመንግስት ትርጉም መስጠትን አስፈላጊት ገልጸዋል፤የተለያዩ ሀገራትን ልምድ ምን እንደሚመስል ተጠይቀው አብራርተዋል፡፡ ሀሳባቸውን ካቀረቡት ምሁራን መካከል ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ፤ ዶ/ር ሶሎሞን ደርሶ፤ ዶ/ር ዘመላክ አየለ፣ ዶ/ር አደም ካሴና ዶ/ር ዮናታን ፍሰሃ ናቸው፡፡
ባለሙያዎቹ ህገመንግስቱ ክፍተት እንዳለው የገለጹ ሲሆን ህገመንግስታዊ ትርጉም በመስጠትን ያለው ክፍተት ሊሞላ ይችላል ብለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ህገመንግስታዊ ትርጉም ሰጥቶ ችግሩን ማለፍ የተሻለ አንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከእነሱ ቀጥሎ የህግ ባለሙያዎች ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን የህገመንግስት ባለሙያዎች ካቀረቡት ሀሳብ ጋር የሚመሳሰል ማለትም፣ የትርጉሙን አስፈላጊት የሚደግፍ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ የህገመንግስት፣የህግ፣ የህገመንግስቱ አርቃቂ አባለትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ሀሳብ እንዲያቀርቡ ተጋብዘውበታል ተብሏል፡፡
ጉባኤው ይህን ያዘጋጀው የዘንድሮው ምርጫ ተራዝሞ “ህገመንግስታዊ ትርጉም” አንዲሰጥ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን ተከትሎ ነው፡፡
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነሀሴ 23 እንዲካሄድ ቀን ቆርጦለት የነበረው “ምርጫ 2012” የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መስራት እንዳልቻለና መራዘም እንዳለበት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሰረት ምርጫ በየ 5 አምስት አመቱ ይሄዳል፤የመንግስትም ሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ስልጣን ዘመን እንደሚያበቃም ይደነግጋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መንግስት እስከ ነሀሴ የሚቆይ አምስት ወር አስቸኳይ ጊዜ አወጅ በማወጁና በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ምርጫ ምን ይሁን የሚል ነገር ስለሌለው፣ የመንግስት ስልጣንን በሚገድበው የህገመንግስቱ አንቀጽ 58(3) አንዲተረጎም ምክርቤት ለጉባኤው አስተላልፏል፡፡
ከአንቀጽ 58(3) በተጨማሪ አንቀፅ 54/1ና እና አንቀፅ 93 ትርጉም እንዲሰጥባቸው ተጠይቋል፡፡
በምርጫ ጉዳይ የፖለቲካ ፖርቲዎች የተለያየ አቋም እያንጸባረቁ ይገኛሉ፡፡ መንግስትን የሚመራው ገዥ ፓርቲ ብልጽግና የህገመንግስት ትርጉም በመስጠት አሁን ካለው ችግር መውጣት ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡ ዋና ተቃዋሚ የሚባሉት ፓርቲዎች ደግሞ “የሽግግር መንግስት ይቋቋም” እና “የፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፋልጋል” በሚሉ የተለያየ አቋሞች ተቃርነዋል፡፡