አሁን ያለው መንግሥት ስልጣኑ ለ1 ዓመት እንዲራዘም ትብብር ፓርቲ ጠየቀ
ለተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት መፍትሔ ያለውን ሀሳብ የፓርቲዎቹ ስብስብ አቅርቧል
ምርጫው እስከ ግንቦት 2013 ሊራዘም እንደሚገባ ኦነግን ጨምሮ የ10 ፓርቲዎች ስብስብ የመፍትሔ ሀሳብ አቀረበ
ምርጫው እስከ ግንቦት 2013 ሊራዘም እንደሚገባ ኦነግን ጨምሮ የ10 ፓርቲዎች ስብስብ የመፍትሔ ሀሳብ አቀረበ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)ን 10 ፓርቲዎችን ያቀፈው ትብብር ለህብረ-ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም (ትብብር) በኮቪድ-19 ምክንያት ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ሕገ-መንግሥዊ ቀውስ (አጣብቂኝ) ለማሻገር ይበጃል ያለውን የመፍትሔ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
የለዉጥ ኃይሉ ጠቅላላ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የሚያስፈልጉ ሪፎርሞችና የህግ ማሻሻያ ዝግጅቶችን በማድረግ በምርጫ 2012 ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ሕዝብን የሚወክል መንግሥት እንደሚመሠረት ተስፋ የተጣለበት ተግባር ሲያከናውን እንደቆየ ትብብር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ይሁንና ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች ባሉበት በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምርጫ እንዳይካሄድ በማድረጉ፣ ይበጃል ያለውን የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረቡን ነው ትብብር የገለጸው፡፡
ለተፈጠረው ችግር በመንግስት እንደ መፍትሔ የተወሰደው ህገ-መንግሥቱን የመተርጎም ስርዓት በመሠረታዊነት የሚመለከተው ክርክር ያለባቸው ወይም አወዛጋቢ የሆኑ አንቀጾችን በመሆኑ በዚህ እንደማይስማማ በመግለጽ ፣ ትብብር የተሸለ ያለውን የራሱን የመፍትሔ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
ባጠቃላይ አሁን ሀገሪቱ ያጋጠማት ፈተና መፍትሔው በሕገ-መንግሥቱ ሊገኝ የማይችል አዲስ አጋጣሚ እንደመሆኑ በአዲስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ብቻ ልንወጣው ይገባል የሚል እምነት እንዳለውም ትብብር ገልጿል፡፡
እናም አሁን ያለዉ መንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካል (Executive body) ለአንድ ዓመት ሥልጣኑ ተራዝሞ እና ጠቅላላ ምርጫው በግንቦት ወር 2013 ተጠናቆ አዲስ የሚመረጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀደም ሲል በተለመደው ጊዜ ስራውን እንዲጀምር ማድረግ የትብብር የመፍትሔ ሀሳብ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በሚከተሉት ሀገራዊ ጉዳዮች ዉስጥ በቀጥታ ተሳትፎ ድርሻ ኖሯቸው ለዴሞክራሲ ግምባታም ሆነ ለሀገር ሰላምና ህልዉና አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግንም ሀሳቡ ይጠይቃል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሳተፉባቸው የተጠየቁት ዘርፎች፡
በዉጭ ግንኙነት አካል ዉስጥ (Council of Foreign Relation) መሳተፍ፣
በብሔራዊ ደህንነት፡- በሀገር ደህንነትና ሰላም ጉዳዮች አካል ዉስጥ (በሀገር ደህንነት፣ መከላከያ፣ ፖሊስ) መሳተፍ-ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ በሆነ መንገድ ማገልገላቸዉን ለመከታተልና ብሎም በሀገር ህልውና ላይ የሚቃጣ አደጋ ቢያጋጥም የጋራ ሀላፊነት ለመዉሰድ እንዲያግዝ፣
የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተቋማት (Democratic Institutions building) ዉስጥ መሳተፍ፣
ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚረዳ ኮሚሽን-ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚረዳ የጋራ አካል በጋራ ለመፍጠር መሳተፍ፣
የተራዘመዉን የጊዜ ገደብ አግባብ ባልሆነ መልኩ በመጠቀም ለሌላ ችግር እንዳይዳርገን የሚቆጣጠር ኮሚቴ ውስጥ መሳተፍ፡፡
ትብብር ለህብረ-ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፈደራልዝም (ትብብር) ከስምምነት የደረሰበት ይህ የፖለቲካ ውሳኔ ሀሳብ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ካጋጠማት ሕግ መንግሥታዊ ቀውስ ሊያሻግራት የሚችልየተሸለ መፍትሔ እንደሆነ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ፣ ምርጫው እንዲራዘም መግባባት ላይ ደርሶ ለዚህም የሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲሰጥ ዉሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡