ምርጫ መራዘሙንና ለተፈጠረው ችግር ሕገ መንግስታዊ ትርጉም እንዲሰጥ መወሰኑን እንደሚደግፍ ትዴፓ ገለጸ
ምርጫ መራዘሙንና ለተፈጠረው ችግር ሕገ መንግስታዊ ትርጉም እንዲሰጥ መወሰኑን እንደሚደግፍ ትዴፓ ገለጸ
የፌዴራል መንግስት ምርጫ ሊያካሂድ እንደማይችል ማስታወቁን ተከትሎ፣ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የትግራይ ክልል የኮሮናን ወረርሽኝ እየተከላከለ ምርጫውን ማካሄድ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ “በክልላችን ምርጫው በሕግ ማዕቀፍ በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከማህበራትና ከህዝብ ጋር በመመካከር የምርጫ ቦርድንም ባሳተፈ ሁኔታ ህጋዊ አፈፃፀም እንዲኖረው ይደረጋል” ሲሉም ሊቀመንበሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የህወሓት ሊቀመንበርን መግለጫ ተከትሎ በክልሉ ተፎካካሪ የሆነው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “በክልል ደረጃ ምርጫ ለማድረግ መወሰንና ማስታወቅ ሕገ መንግስታዊ አይደለም ይህ የሚሆንበት የሕግ አግባብ የለም” ብሏል ፓርቲው፡፡
የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ “ሀገሪቱን ለዚህ ቀውስ የዳረጋት ራሱ ህወሓት ነው፣አሁንም የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና ከሕግ ውጭ በክልል ደረጃ ምርጫ አደርጋለሁ በማለት የትግራይን ህዝብ እያደናገረ ነው” ብለዋል፡፡
አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዚህ ዓመት ነሐሴ መጨረሻ ላይ ሊደረግ የነበረው ምርጫ እንደማይደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉን ፓርቲያቸው እንደሚደግፍም ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ትኩረት መደረግ ያለበት የኮሮና ቫይረስን መከላከል ላይ መሆኑን ፓርቲያቸው እንደሚያምንም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ወቅት “ምርጫ በክልል ደረጃ እናደርጋለን ማለት እጅግ አሳፋሪ ነው” ያሉት ሃላፊው፣ የህም “ህወሓት ላለፉት ዓመታት ሲሰራ የነበረውን ሀገራዊ ጥፋት ስለመቀጠሉ አንዱ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮሮና ቫይረስ እና ምርጫ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ከሕወሓት የተወከሉት አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) መንግስት ቀድሞውንም ቢሆን ምርጫ ለማድረግ ፍላጎት እንዳልነበረው መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ደግሞ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ መንግስት በግልጽ ምርጫዉን የማድረግ ዝግጁነት እንደነበረው እና ምርጫ ለማድረግ ቀን ተቆርጦ እንደነበር ካብራሩ በኋላ በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት መንቀሳቀስ እንኳን እንደማይችሉ በመግለጽ ህወሓትን ተችተዋል፡፡ ሰላማዊ ፖሊቲካ ለማራመድ ሕወሓት መጀመሪያ በክልሉ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መነጋገርና ዴሞክራሲን መለማመድ እንደሚገባው መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡
ከዚህ ውይይት በኋላ ነው የሕወሓት ሊቀመንበር በክልሉ ምርጫ እንደሚደረግ የገለጹት፡፡
የትዴፓ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ “ ምርጫን በክልላችን እናደርጋለን ከሚለው የሕግ ጥሰት ባለፈ ፓርቲያችን በክልሉ በሚያከናውናቸው ፖለቲካዊ ስራዎች ላይ ጫና አየተፈጠረበት ነው” ነው ብለዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም “ትግራይን ከኢትዮጵያ እንገነጥላለን በማለት ህዝብን እያደናገሩ ነው” ያሉት አቶ ሙሉብርሃን የህወሓት አባላትና አመራሮች አሁን ላይ ሀገር የማፍረስ ስራ እየሰሩ ነው”ይላሉ፡፡
በትዴፓ አባላትና አመራሮች ላይም የሥነ ልቦናና የአካል ጥቃት እየደረሰ መሆኑን አቶ ሙሉብርሃን ገልጸዋል፡፡ ከሰሞኑም የትዴፓ አመራር አባል አቶ ብርሃነ አርአያ በመቀሌ ከተማ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የገለጹት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ የፓርቲያቸው አመራር ድብደባው የተፈጸመባቸው “በህወሓት የደሕንነት ሰዎች” ነው ሲሉ ለአል ዐይን አስታውቀዋል፡፡
ህወሓት ሕገ መንግስቱን ሽፋን በማድረግ ህዝብን ለችግር እንደዳረገ የሚገልጹት ኃላፊው አሁን ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሕገ መንግስት ትርጉም መሰጠት አለበት በሚል የቀረበው ሃሳብ በትዴፓ በኩል ተቀባይነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታና ትዴፓ ያቀረባቸውን ቅሬታዎች በተመለከተ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡን በእጅ ስልካቸው ላይ የደወልንላቸው የክልሉ መንግስትና የፓርቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ስልክ ባለመመለሳቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡