“ፖለቲከኞች ሥልጣን እንዲይዙ ወጣቶች ማለቅ የለባቸውም…” ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)
”ሥልጣን እንደ ድግስ ትሩፋት ለሁሉም ይዳረስ የሚለው አካሄድ ሀገርን ወደ ኋላ ይጎትታል“
ሕገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ለሥልጣን የሚደረግ እንቅስቃሴን መንግስት እንደማይታገስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ
ሕገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ለሥልጣን የሚደረግ እንቅስቃሴን መንግስት እንደማይታገስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ
ሕገ መንግስቱ ከደነገገው ሥርዓት ውጭ ያለምርጫ እንዲሁም ሕገ መንግስታዊ ዕውቅና በሌለው ሕገ ወጥ ምርጫ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የተራዘመውን ምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክተው በቪዲዮ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ መንስቱትን ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ ይህም መንግስት የማይደራደርበት ሕገ መንግስታዊ ግደታው እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ምርጫ ሳይካሄድ እንዲሁ ተጠራርቶ ስልጣን የሚያከፋፍል ምንም አይነት ሕገ መንግስታዊ አካሄድ እንደሌለም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በንግግራቸው ያነሱት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫንና የኮሮና ቫይረስን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ አሁን ላይ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት የሚጠይቁ ሃይሎች ያቀረቡት አማራጭ ትክክለኛ እንዳልሆነና የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ስለሆኑ ብቻ ሥልጣን ይገባኛል የሚለው ጥያቄ ተገቢነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግስታዊ ስላለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡
“‘ስልጣን በምርጫ ብቻ ይገኛል’ የሚለውን መርህ በመጣስ ሥልጣን እንደ ድግስ ትሩፋት ለሁላችንም ይዳረስ“ የሚለው አካሄድ፣ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ወደ ጎን በመተው ከህዝብና ከሀገር ይልቅ የሥልጣን ፍላጎትን የሚያስቀድም አስተሳሰብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ የተመረጠ መንግስት እያለ ያልተመረጡ ፓርቲዎች ተሰባስበው መንግስት የሚመሰርቱበት ምንም አይነት ህጋዊነት የለውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ከ100 በላይ ፓርቲዎች ተደራድረውና ተስማምተው ወደ ፖለቲካዊ መፍትሄ እስኪመጡ ድረስ ምርጫው የሚራዘምበት ችግር ተፈቶ ለህጋዊ ምርጫው ቀን ይደረሳል ያሉት ዶ/ር ዐቢይ በኢትዮጵያ ያለው ሪፎርም እንጂ አቢዮት አይደለም ብለዋል፡፡ የሽግግር መንግስት የሚለው ሀሳብ ከህግ አንጻር ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም በንድፈ ሀሳብም ሆነ ከሽግግር ተሞክሮ አንጻር ለኢትጵያ የሚበጅ አይደለምም ብለዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ሥጋት ባለበትና የቀጣናችን ሁኔታ ለሀገር ሉዓላዊነት ሥጋት በደቀነበት ወቅት የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን ማለት ሃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስታወቁት፡፡ አካሄዱም ህገ ወጥ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ነው ብለዋል፡፡
ሕገ መንግስቱ ከደነገገው ሥርዓት ውጭ ያለምርጫ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ ዕውቅና በሌለው ሕገ ወጥ ምርጫም ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄን መሰል ህገ-ወጥ ተግባርን በመከላከል ሕገ መንግስቱን ለመጠበቅ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ ይህም መንግስት የማይደራደርበት ሕገ መንግስታዊ ግደታው ነው ብለዋል፡፡
በሕገ መንግስቱና በሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ካልሆነ በስተቀር “የጨረባ ምርጫ” ለማድረግ መነሳት ሀገርንና ህዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መንግስት ሀገርንና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ሥልጣን የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች የሃሳብ ክርክሮቻቸውን ወጣቱንና እናቶችን በማይጎዳ መልኩ እንዲያደርጉ ያሳሰቡት ዶ/ር ዐቢይ “ፖለቲከኞች ሥልጣን እንዲይዙ ወጣቶች ማለቅ፣እናቶች ማልቀስ ቤቶች መፍረስ ፣ህዝብ መፈናቀል የለባቸውም” ብለዋል፡፡
ሕገ መንግስታዊ ትርጉም ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ከሌሎች ሕገ መንግስታዊ አማራጮች በተሸለ መልኩ ይፈታዋል ብሎ መንግስት የሚያምነው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዐቢይ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዩን በአጽንኦት እንዲከታተልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡