በኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ከተጀመረ 2 የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ደግሞ 9 ዓመት ሆኗል
በኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ከተጀመረ 2 የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለ ደግሞ 9 ዓመት ሆኗል
ከሁለት ዓመታት በፊት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ልክ በሰባተኛው ዓመት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁለት ዓመታት ቆይታ ሙሉ በሙሉ በፈታኝ ሁነቶች የታጀበ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ለውጡን ከሚፈታተኑ ግጭቶች እና የተለያዩ ሴራዎች የሀገሪቱ ፖለቲካ እንዳይረጋጋ አድርገው የቆዩ ሲሆን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ደግሞ በተለይም ከግብጽ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ሌላ የውጥረት ምንጭ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በነዚህ ፈታኝ ዓመታት፣ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው እና ማህበራዊ መስኮች ይበል የሚያሰኙ ጠንካራ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የግድቡን ዘጠነኛ ዓመት እና የለውጡን ጉዞ ሁለተኛ ዓመት በማስመልከት ባስተላለፏቸው መልእክቶች በርካታ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡
“ኮሮናን እንከላከላለን ፤ ግድቡን እንጨርሳለን”
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ዘጠነኛ ዓመት በሚከበርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ሁለት ጉልህ ፈተናዎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡ አንደኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ራሱ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን የተመለከተ ጉዳይ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከ200 በላይ ሀገራትን ያዳረሰ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዮን እየተጠጋ ነው። የሟቾች ቁጥር ደግሞ ከ 48000 በልጧል፡፡
በኢትዮጵያ ደግሞ እስካሁን 29 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡
በበሽታው ምክንያት ምርጫ 2012ም ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል፡፡ መንግስት በአጭር ጊዜ አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ፍትሃዊና ተዓማኒ ምርጫ አደርጋለሁ ቢልም ወቅታዊው ኮሮና ጣልቃ በመግባት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንዳይካሔድ አድርጓል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን በመልእክታቸው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህብረተሰቡም የሚያደርገውን ጥንቃቄ እና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ግድቡን በተመለከተ ደግሞ “በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከምትጠነቀቅላቸውና በስስት ከምታያቸው ጸጋዎቿ ሁለተኛው የሕዳሴ ግድባችን ነው” ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግድቡን ሲጎበኙ
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ለግድቡ እውን መሆን የሚያደርጉትን ርብርብ ያደነቁት ጠ/ሚኒስትሩ “የሕዳሴ ግድባችን ከዕለት ጉርሳችን ቀንሰን በተባበረ ክንድ እየገነባን እዚህ ያደረስነው ብቻ ሳይሆን የማድረግ ዐቅማችንን ያሳየንበት ትልቁ ጸጋችን ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
”ለግድባችን ከፍ ያለ ግምት የምንሰጠው አንድም የሉዓላዊነታችን ምልክት፣ ሁለትም የትሥሥራችን ገመድ በመሆኑ ጭምር ነው” ያሉም ሲሆን የፊታችን ክረምት ግንባታው ተገባዶ የውኃ ሙሌት እንደሚጀመር አብራርተዋለ፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በዚህ ወቅት መከሰቱ በግንባታው ሂደት ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ጉልህ ቢሆንም፣ ”በወረርሽኙ ምክንያት የግድብ ባለቤት የመሆን ጉዟችን ማዝገም የለበትም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ሁለተኛው የለውጥ ዓመት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ወደ መሪነት ካመጣው ለሶስት ዓመታት ያክል የዘለቀ ህዝባዊ አመጽ በኋላ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ሁለተኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡
ለውጡ በአንድ በኩል ፈተናና ስጋት በሌላ በኩል ተስፋ እንደሚታይበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡
የለውጡ ስጋትና ፈተናነት የተጠቀሰው አንዱ ጉዳይ አሁን ላይ የመላው ዓለም ስጋትና ፈተና የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው፡፡
በሶማሌ ክልል፣ በወለጋ እና በሌሎች የምእራብ ኦሮሚያ ክፍሎች የነበሩ በታጠቁ ኃይሎች የተፈጸሙና በመፈጸም ላይ ያሉ ወንጀሎች እና በህዝብና መንግስት ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ በአማራ ክልል እና በመከላከያ አመራሮች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ማንነትን መሰረት ካደረገ ግድያ እስከ መንደር ማቃጠል የሚደርሱ የጥፋት ርምጃዎች የለውጡ ጉዞ ካስተናገዳቸው ስጋቶች እና ፈተናዎች መካከል ናቸው፡፡
”የለውጥ ጉዞው በየጊዜው የሚገጥሙትን ጋሬጣዎች ከመሻገር ባለፈ የተለያዩ የሪፎርም ተግባራትን ለማከናወን የተንቀሳቀሰበት ወሳኝ ወቅትም ነበር” ብለዋል ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
ሀገሪቱን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ማለፋቸው እንደማይቀር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
“ተባብረን፣ ተደምረን፣ በአንድነት ወቅታዊ ፈተናችንን እንሻገራለን፤ የምንመኛትን፣ የምንጓጓላትን፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን እንገነባለን፡፡ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፣ መስሪያ ቤቶችና ድንበሮች ይከፈታሉ፤ የተቀዛቀዘ ኢኮኖሚያችን ዳግም ያንሰራራል፡፡ ላልተወሰነ ጊዜ የምናደርገው መራራቅ በመቀራረብ ይተካል፡፡ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ወደነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ሞትም በሕይወት ይሸነፋል” ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ በመግለጫቸው ማብቂያ ላይ፡፡