በጉባዔው የሚለዩ ባለሙያዎች በተያዙ ጭብጦች ዙሪያ በመጪው ቅዳሜ እና ሰኞ ሙያዊ ምስክርነትን ይሰጣሉ ተብሏል
የሕገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሙያዊ አስተያየቶች ጥሪ አቀረበ
ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ የቀረበለት የሕገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የሙያዊ አስተያየቶች ጥሪን ለተቋማትና ባለሙያዎች አድርጓል፡፡
ጥያቄው ከደረሰው ከሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ/ም ጀምሮ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ጥያቄውን ለመመርመር አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ጉባዔው በቀረበለት ጥያቄ መሰረት “ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ”ን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ይችል ዘንድ ነው ጥሪውን ያደረገው፡፡
የሚቀርቡ ሙያዊ አስተያየቶች ሊያሟሏቸውና አቅራቢ ባለሙያዎቹ ሊከተሏቸው የሚገቡ ስርዓቶችን የተመለከቱ ዝርዝር የስነ ምግባር መስፈርቶችንም አውጥቷል፡፡
የተለያዩ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የህግ በተለይም የህገ መንግስት ባለሙያዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በጥሪው መሰረት እንዲሳተፉም ጋብዟል፡፡
በጉባዔው የሚለዩ ውስን ቁጥር ያላቸው የህግ ባለሙያዎች በተያዙ ጭብጦች ዙሪያ ጉባዔው ፊት በመቅረብ ለህዝብ ይፋ በሚሆን መድረክ ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ/ም ከ3 እስከ 7 ሰዓት እንዲሁም ሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ/ም ከ8 እስከ 12 ሰዓት ወደፊት በሚገለጽ ስፍራ የሙያ ምስክርነት የሚሰጡ ሲሆን ህዝቡ ጉዳዩን እንዲከታተል በጉባዔው በኩል ጥሪ ቀርቧል፡፡
ባለሙያዎችን ማሳተፉ የስራ ሂደቱን ተዓማኒነት እና የሚሰጠውን “ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሃሳብ” ቅቡልነት ለመጠበቅ እንዲሁም አዲስ ህገ መንግስታዊ ባህልን ለማዳበር ነው እንደ ጉባዔው ገለጻ፡፡
የህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልግም የሚል ውሳኔ ላይ ከደረሰ የሚሰጠው “ውሳኔ” ሲሆን ያስፈልጋል የሚል ከሆነ ግን የሚሰጠው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚጸድቅ “የውሳኔ ሃሳብ” እንደሆነም አጣሪ ጉባዔው አስታውቋል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት 6ኛውን ሃገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል በማሳሰብ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ያጸደቀው የተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ/ም ባደረገው ልዩ ስብሰባ የምርጫውን ቀጣይ ሂደት በተመለከተ በተመረጡ 3 አንቀጾች ላይ የህገ መንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡
ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሆነውና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት (ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ) እና ምክትል ፕሬዝዳንት (አቶ ሰለሞን አረዳ) ሰብሳቢነት የሚመራው ጉባዔው በ1993 ዓ/ም የተቋቋመ ሲሆን በፕሬዘዳንቱ/ቷ የሚሾሙ ስድስት የህግ አማካሪ አባላት አሉት፡፡