የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚያደርጉ ፖለቲካዊ እውነታዎች አሁን ላይ የሉም
“ህወሓት አሁን ያለውን አቋም የያዘው ስለሚያዋጣው ሳይሆን በደረሰበት ፖለቲካዊ ኪሳራ ነው”- ዛዲግ አብርሃ
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለሕገ-መንግሥቱ ሞቻለሁ፤ የሕገ-መንግሥቱ አንዲት አንቀፅ ብትሸራረፍ ወዮላችሁ” እያለ ቢያስፈራራም ሕገ-መንግሥቱን እየጣሰ ያለው የመጀመሪያው ፓርቲ ራሱ ነው ሲሉ ለዘመን መፅሄት ገልጸዋል፡፡
ህወሓት ከጸደቀበት ጊዜ አንስቶ ሕገመንግሥቱን በግላጭ እየጣሰ የመጣ ፓርቲ ነው ያሉት አስተባባሪ ሚኒስትሩ ሰሞኑንም ባወጣው መግለጫ ይህንኑ አካሄዱን አስመስክሯል ብለዋል።
ይህን የሚያደርገው ደግሞ “ስለሚያዋጣው ሳይሆን በደረሰበት ፖለቲካዊ ኪሳራ” ምክንያት እንደሆነ ነው አቶ ዛዲግ የተናገሩት፡፡
በተፎካካሪ ፓርቲዎች የቀረበው የሽግግር መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት የሚል አማራጭ በግልቡ ሲታይ ችግር ያለበት አይመስልም ያሉም ሲሆን የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚያደርጉ ፖለቲካዊ እውነታዎች አሁን ላይ እንደሌሉ እና የሽግግር መንግሥት ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ህወሓት 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ የማይካሄድ ከሆነ “የትግራይን ራስ በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ እውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሥራዎች በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ” መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡
አቶ ዛዲግ ከአሁን ቀደም ከፍተኛ የህወሓት አመራር እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡