“ወደ ሃምዳይት እና ሓሻባ በሸሹ ሰዎች ከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው”- የሑመራ እና አካባቢው ነዋሪዎች
ነዋሪዎቹ በሱዳን የስልክ መስመሮች እየደወሉ እንደሚያስፈራሩዋቸው እና እንደሚዝቱባቸውም ጭምር ነው የተናገሩት
“በአካባቢዎቹ የተጠናከረ ጸጥታ ሓይል በመኖሩ የሚያሰጋ ነገር የለም”- ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
“ወደ ሃምዳይት እና ሓሻባ በሸሹ ሰዎች ከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው”- የሑመራ እና አካባቢው ነዋሪዎች
በወልቃይት እና ሁመራ የተለያዩ አካባቢዎች ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ ሸሽተው ወደ አዋሳኝ የሱዳን ድንበራማ አካባቢዎች ከገቡ ስደተኞች ከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው ሲሉ አንዳንድ የሑመራ እና ማይካድራ አካባቢ ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናገሩ፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ነዋሪዎቹ “ወደ ሃምዳይት እና ሓሻባ ሸሽተው በገቡ ሰዎች የ ‘እንመጣላችኋለን’ ማስፈራሪያ እየደረሰን ነው” ብለዋል፡፡
ሃምዳይት እና ሓሻባ ከሰላ እና ገዳሪፍ ተብለው በሚጠሩ የሱዳን አጎራባች ክልሎች የሚገኙ ከተሞች ናቸው፡፡
ሃምዳይት ከሑመራ በቅርብ ርቀት ምናልባትም ከ20 በማይበልጡ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በእግር ለመጓዝ የሚችሉትም ነው፡፡
ሱዳን፣ኢትዮጵያ እና ኤርትራን የሚያገናኝ ወሳኝ አካባቢም ነው-ሃምዳይት፡፡
ህወሓት የኢትዮጵያን የሃገር መከላከያ ሰራዊት ማጥቃቱን ተከትሎ በሁመራ እና በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ውጊያ ሸሽተው ወደ ሱዳን የሄዱ ብዙዎችም በብዛት በዚሁ አካባቢ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡
ሓሻባም እንደዚያው ነው፡፡ በማይካድራ ከተፈጸመው እልቂት በኋላ ብዙዎች ሸሽተው ወደ ሓሻባ ገብተዋል፡፡
ወደዚህ አካባቢ ካቀኑት ብዙዎቹ “የእልቂቱ ፈጻሚ የሆኑ የትግራይ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላት ናቸው” ስማቸውን ለመጥቀስ እንዳልፈለጉት የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጻ፡፡
በአካል እና በግብርም “የምናውቃቸው የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላት” ወደ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎቹ ገብተዋል የሚሉት ነዋሪዎቹ “ከአሁን በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ተደራጅተው እንዳያጠቁን ሰግተናል” ብለዋል፡፡
በሱዳን የስልክ መስመሮች እየደወሉ እንደሚያስፈራሩዋቸው እና እንደሚዝቱባቸውም ጭምር ነው የገለጹት፡፡
የታጠቁትን መሳሪያ ሸሽገው በየበረሃው ቀብረው ነው ወደዛ የሄዱትም ነው ነዋሪዎቹ የሚሉት፡፡
የአማራ ክልልም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት ጉዳዩን አውቆ ሁኔታዎችን በቅርበት እንዲከታተል እና እንዲጠብቃቸውም ጠይቀዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ የነዋሪዎቹን ስጋት በተመለከተ የአማራ ክልል የሰላምና ደህንነት ግንባታ ቢሮ እና የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
በፌዴራል መንግስት በኩል ያለውን ዝግጁነት ምን ይመስላል ሲል ግን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴን ጠይቋል፡፡
“በአካባቢዎቹ የተጠናከረ ጸጥታ አለ”ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራሉ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ የሰራዊት አባላት በስፍራው እንደሚገኙ ገልጸው“እንደዚህ አይነት ችግሮች አይፈጠሩም” ብለዋል፡፡
የነዋሪዎቹን ስጋት በተመለከተ “ዛቻዎቹ ለማስፈራሪያ የተባሉ ሊሆኑ ይችላሉ እንጂ ይህንን ለማድረግ አይችሉም” ሲሉ የመለሱም ሲሆን ድንበር ላይ ከፍተኛ ጥበቃ መኖሩን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሊያጠቁ የሚችሉበት እድል እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን “እጅግ አሰቃቂ ምናልባትም በጦር ወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ነው”ባለው እና ብሄር ተለይቶ በአማራዎች ላይ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን በተፈጸመው ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ጅምላ መቃብሮች እስካሁን ድረስ እየተገኙ እንደሆነም ይታወቃል፡፡