መንግስት በትግራይ ባሉ ዩንቨርሲቲዎች ያሉ ተማሪዎችን ደህንነት እንዲያስከብርም ኮሚሽኑ አሳስቧል
በአዲስ አበባ የታሰሩ ጋዜጠኞችን ጉዳይ እየተከታተለ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
በአገሪቱ ባሉ ወቅታዊ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ስራዎች ዙሪያ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ኢሰመኮ ክልል የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብሏል።
የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው፣ በክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውም ገልጿል ኮሚሽኑ።
መንግስት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ ይገባል ያለው ኮሚሽኑ በክልሉ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ ይገባልም ነው ያለው፤ የመሰረተ ልማቶቹ መመለስ በክልሉ ስላለው ተጨባጭ የፀጥታ እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሁኔታ በቂ መረጃ ለማግነት እንደሚረዳ በመጠቆም።
በክልሉ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር መፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ሊሆኑ ይገባል ብሏል።
ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ተግባር መሆኑንም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት ሊሆኑ ይገባል ያለው የኮሚሽኑ መግለጫ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የትግራይ አከባቢዎች የመብራት፣ የስልክ እና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ መሆኑን ገልጿል።
የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን እንዳባበሰውም አስታውቋል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብአዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳው ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አለመቻሉንም ገልጿል ኮሚሽኑ በመግለጫው።
በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ እገኛለሁም ብሏል ኮሚሽኑ።
ድርጊቱ በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር ነው ሲል ኢሰመኮ በመግለጫው አስታውቋል።
በተጨማሪም፣ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግስት ግዴታ መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው ብሏል።
የተኩስ አቁሙ በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሰረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብአዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት ያግዛልም ብሏል ኮሚሽኑ።
በተጨማሪም ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን እንደሚገባም ተገልጿል።
በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡም ኮሚሽኑ አሳስቧል።