የኢትዮጵያ መንግስት የተመድ መርማሪ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንዲሰራ አልፈቅድም ማለቱ ይታወሳል
በትግራይ የተፈጸመው ዓለም አቀፍ ወንጀል ሊጣራ ይገባል ሲሉ የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ተናገሩ፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን በጦርነቱ ከተፈጸሙ ወንጀሎችና ተጠያቂነት ጋር በተያያዘ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ፍትህ ሊረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡
- መንግስት የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ መበሳጨቱን ገለጸ
- ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በመንግስትና በህወሓት መካከል ስለተፈረመው የሰላም ስምምነት ምን አሉʔ
የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ የሚያደርግ የባለሙያዎች ቡድን የጀመረውን ምርመራ እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
“ቡድኑ ወደ ትግራይ አልመጣም ገና፤ ምርመራው መካሄድ አለበት፤ ፍትህም ሊነግስ ይገባል” ብሐዋል ሊቀመንበሩ።
ሊቀመንበሩ ይህንን ያሉት የስራ ጊዜውን ለአንድ ዓመት ያራዘመውን መርማሪ ቡድን የተቃወመው የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ በጠየቀበት ማግስት መሆኑ ነው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቀናት በፊት በተካሄደው የህብረቱ ስራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ሀገራት በተመድ የተቋቋመው ቡድን እንዲፈርስ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥያቄ እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡
ቡድኑ በፕሬቶሪያ የተደረሰውን ስምምነት የሚያደናቅፍና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት እና የመፍትሔ ሀሳቦች እንዳይተገበሩ የሚያደርግ እንደሆነም አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ መርማሪ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ እንዲሰራ እንደማትፈቅም ተናግረዋል የውጭ ጉዳየ ሚኒስትሩ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ጫና ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡
በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር የተወያዩት የጀርመን እና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዋና አጀንዳ ይህ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
የጀርመኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤርቦክ የጉብኝታቸው ዋና ዓላማ “ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላምና ለሰብዓዊ መብት ረገጣ ተጠያቂነት ለማስፈን” በምታደርገው ጉዞ ለመደገፍ እንደነበር መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አስደንጋጭና አሳዛኝ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ “ያለፍትህ ዘላቂ ሰላም የለም”ም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በጦርነቱ እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል።