ታዋቂው ኢራቃዊ ፓለቲከኛ አል ሳድር፤ ራሱን ከፖለቲካው እንዳገለለ ማስታወቁን ተከትሎ በሃገሪቱ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል
የአል ሳድር ደጋፊዎች ቤተ መንግስት ሠብረው መግባታቸውን ተከትሎ በባግዳድ ሰዓት እላፊ ታውጇል
አል ሳድር ጥቅምት ላይ የተካሄደውን ምርጫ ቢያሸንፍም መንግስት ለመመስረት አልቻለም
ኢራቃዊው የሺዓ እስልምና መሪ እና ፖለቲከኛ ሙቅታዳ አል ሳድር ራሱን ከፖለቲካው እንዳገለለ ማስታወቁን ተከትሎ በኢራቅ ከፍተኛ ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ።
በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲከኛው ተከታዮች ውሳኔውን በመቃወም ወደ ብሔራዊ ቤተመንግሥት ሰብረው ገብተዋል። አዲስ ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሰየም ተሰብስቦ የነበረውን የሃገሪቱን ፓርላማም ተቆጣጥረዋል።
ይህን ተከትሎ በአስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አል ካዲሚ ስብሰባውን በትነው ወጥተዋል። በቤተ መንግስቱ እና በአካባቢው ከባድ ጥበቃ እየተደረገም ሲሆን በባግዳድ ሰዓት እላፊ ታውጇል።
ስልጣን ባይዝም በፖለቲካ ተሳትፎው ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው አል ሳድር "በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ላለመግባባት ወስኛለሁ” በሚል ነበር ራሱን ከፖለቲካው ማግለሉን በይፋዊ የትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጹ ያስታወቀው።
የፖለቲካ ተቋማቱን ጨምሮ በፓርቲው ሳድሪስት ንቅናቄ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሁሉ እንደሚያቆምም አስታውቋል።
አል ሳድር ባሳለፍነው ጥቅምት የተካሄደውን ሃገራዊ ምርጫ 73 የፓርላማ ወንበሮችን በማግኘት በአብላጫ አሸንፏል። ሆኖም ያገኘው ድምፅ መንግስት ለመመስረት አላስቻለውም።
በኢራን እንደሚደገፉ ከሚነገርላቸው ሌሎች የሺዓ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀናጅቶ መንግስት መመስረቱንም አልፈለገም።
ወደ ፓርላማው የገቡ የፓርቲ አጋሮቹ ምርጫው እንዲደገም በማሳሰብ ራሳቸውን ከፓርላማው አግልለውም ነበር። ራሱ አል ሳድር ሳይቀር በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ በጋራ እንዲሰግዱና እንዲጸልዩ አድርጎ ነበሮ። ሆኖም ምንም የተሳካም ሆነ የተለወጠ ነገር የለም።
በዚህም ራሱን ከፖለቲካው ለማግለል መወሰኑን አስታውቋል። ሆኖም ውሳኔው በደጋፊዎቹ ዘንዶ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። ቁጣው ይበልጥ ተባብሶ ወራትን ያለ መንግስት የዘለቀችውን ኢራቅን የከፋ ችግር ውስጥ እንዳይከታት ተሰግቷል።