የአይ ኤስ አይኤስ መሪ የነበረው አቡ በካር አልባግዳዲ ከሁለት አመት በፊት በአሜሪካ ጥቃት መገደሉ ይታወሳል
የኢራቁ ጠቅላይ ሚንስትር ሙስጠፋ አል ካዛሚ አሸባሪው ሳሚ ጃሲም ፣ በአይ ኤስ አይኤስ ድርጅት የፋይናንስ ተቆጣጣሪ እና የተገደለው የድርጅቱ መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ ምክትል መያዙን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አል-ካዘሚ በትዊተር ገጻቸው ላይ የኢራቅ የጸጥታ ሀይል በሀገሪቱ እየተካሄደ የነበረውም ምርጫ በጥብቅ እየተከታተለ በነበረበት ወቅት የአልባግዳዲን ምክትል ሳሚ ጃሲምን ይዘዋል ብለዋል፡፡
ሳሚ ጃሲም የአይ ኤስ አይ ኤስ የገንዘብ ተቆጣጣሪም እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተያዘበትን ቦታ ግን አልተናገሩም፡፡
አሜሪካ በፈረንጆቹ 2019 በሰሜናዊ ሶሪያ ባደረሰችው ጥቃት የአይ ኤስ አይኤስ መሪ የነበረው አቡበከር አልባግዳዲ ተግድሏል፡፡ በወቅቱ ግድያው አለምን አነጋግሯል፡፡
የአል ባግዳዲ መገደል አሜሪካን በወቅቱ ሲመሩ ለነበሩት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትልቅ ድል ነው ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡
በሽብር የተፈረጀው አይ ኤስ አይኤስ በመካከለኛው ምሰራቅ ብዙ ጥፋት ካጠፋ በኋላ አሁን በአፍሪካ ሱዳንን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የሽብር ተግባር እየፈጸመ ይገኛል፡፡